አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአፍሪካን የጤና ሥርዓት በራሳችን የፋይናንስ ዐቅም የምንገነባበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን አሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮና ለቀጣይ የአህጉራችን የጤና አቅጣጫ ያለንን ቁርጠኝነት አጋርተናል ብለዋል።
የውጭ ርዳታ እየቀነሰ መምጣቱ ለአህጉራችን ትልቅ ፈተና ቢሆንም በራሳችን ዐቅም ላይ የተመሠረተ፣ የጸና እና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ግን ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሮልናል ነው ያሉት።
ጉባዔው በፈረንጆቹ በ2030 ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን፣ ቲቢንና ወባን ከኅብረተሰብ ጤና ሥጋትነት የምናስወግድበትን፣ መከላከል የሚቻል የእናቶችና ሕፃናት ሞትን የምንገታበትን እና ዘላቂ የፋይናንስ ዐቅማችንን የምናጠናክርበትን አህጉራዊ ፍኖተ ካርታ የምንቀርጽበት የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ራስን የመቻል ሀገራዊ ርዕይን መሠረት በማድረግ በጤናው ዘርፍ ያሳካቻቸውን ተሞክሮዎች በመድረኩ ማካፈሏን አንስተዋል፡፡
አፍሪካ በራሷ ዐቅም የሚመራ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል በቂ ዕውቀት፣ ተቋማትና ተሞክሮ እንዳላትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በጤናው መስክም አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገን የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር ብቻ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እንዲሁም ከአባል ሀገራት ጋር በመተባበር ጤናማና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።