የመደመር መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም የጸና እምነት አላቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ የውጭም ሆኑ የውስጥ ጠላቶች በተነሡ ጊዜ አስቀድመው የሰላምን አማራጭ ይፈልጋሉ፡፡
ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እስከጥግ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ የሰላምን አማራጭ አብዝተው የሚፈልጉት ጦርነት አውዳሚ መሆኑ ስለሚገባቸው ነው፡፡
የሰላም አማራጮች ተሟጥተው ማለቃቸውን ሲመለከቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንደ አራስ ነብር ተነሥተው ጠላቶቻቸውን አደብ ያስገዛሉ፡፡
የጥንትም የቅርብም ታሪካችን ይህንን ይመሰክራል፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በፊት በትግራይ ተፈጥሮ የነበረው ሁኔታ ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት የመደመር መንግሥት የሰላም አማራጮችን ሁሉ ሞክሯል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች መክረዋል፡፡ እናቶች እያለቀሱ ለምነዋል፡፡ የጦርነት ነጋሪት ከልክ በላይ እየተጎሰመ እንኳን በወቅቱ የትግራይን ክልል ከሚመሩ አካላት ጋር የነበረው ግንኙነት እንዳይቋረጥ የመደመር መንግሥት ትዕግሥት አስጨራሽ መንገድ ተጉዟል፡፡
የተለያዩ ወገኖች መንግሥት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዲጠቀም እየወተወቱት እንኳን ለውይይትና ለፖለቲካዊ ንግግር ቅድሚያ በመስጠት ከልክ በላይ ትችቶችን አስተናግዷል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት የኃይል የበላይነት እንዳለው እያረጋገጠ እንኳን ለትግራይ ሕዝብ ሲል ጦርነትን ለማቆምና ከጦርነት ቦታዎች ለመውጣት ቆራጥ ውሳኔዎችን ወስኖ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ጦርነት ውስጥ ሆኖ እርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እንዲደርስ መንገዶችን ከፍቶ አሳልፏል፡፡ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በሄዱበት እየቀሩ እንኳን ከሕዝብ የሚበልጥ የለም በሚል እየታገሰ እርዳታ እንዳይቋረጥ አድርጓል፡፡
ይህ ሁሉ ተደርጎ የሚፈለገው ሰላም ባለመምጣቱ ወደ ግጭት ተገባ፡፡ በዚህም የተነሣ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲፈጽም መንግሥት ተገድዷል፡፡ መንግሥት ተገድዶ በገባበት በዚያ ጦርነት የደረሰውን ኪሣራ ከትግራይ ሕዝብና ከክልሉ መንግሥት በላይ የሚያውቀው የለም፡፡ ጦርነትን ብቸኛ አማራጫቸው ያደረጉ ኃይሎች የትግራይን ወጣቶች ለእሳት ማግደዋቸዋል፡፡ የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ አውድመዋል፡፡
በጦርነቱ መጨረሻ የመደመር መንግሥት ሁሉን ነገር በኃይል ለመፈጸም የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና ነበረው፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑ ስለታመነበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም አድርጓል፡፡
ይህንንም ያደረገው ከመደመር እሳቤ በመነጨ ምክንያት ነው፡፡ በምንም መልኩ ለትውልድ ቂምና በቀልን ማውረስ የለብንም፤ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊን ይፈጥራል፤ ሰላም ግን ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፤ መጪው ትውልድ በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ውስጥ ከሚያድግ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርገው የሰላም ትርክት ውስጥ ቢያድግ ይሻላል በሚል የተደረገ ነው፡፡
ለተጎዱ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚያገግሙበት ፋታ ለመስጠት የተሰጠ ዕድልም ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ሀገርንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሲባል የተከፈለ መሥዋዕትነት ነው፡፡
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መንግሥት በሆደ ሰፊነትና ቁስሉ እንዲሽር ካለው ፍላጎት ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የመደመር መንግሥቱ ልዑክ ነበር፡፡ ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል፡፡
የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር ከተልዕኮ በላይ ተጉዟል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል፡፡ የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን እያገዘ፤ አንዳንድ ነገሮችን ችሎ እያለፈ፤ አንዳንድ ነገሮችን እየመከረ፤ አንዳንድ ነገሮችንም ራሱ እየሠራ የሰላም ስምምነቱ በተሟላ ልኩ በሂደት እንዲፈጸም ለማድረግ ሞክሯል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአንዳንድ ነገሮች ወደኋላ እየቀረና ስምምነቱን በተሟላ ሁኔታ ሳይፈጽም እያነከሰ እንኳን ለክልሉ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ የመደመር መንግሥት አላቋረጠም፡፡
ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል፡፡ አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ ሠርቷል፡፡ የመደመር መንግሥት በዚህ ረገድ የነበረው አበርክቶ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፤ የአካባቢ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፤ በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር።
መንግሥት ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ እነዚህን ሁሉ አቋሞችና ተግባራት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ በሚገባ ያውቃል፡፡
ይህ ሁሉ ቢደረግም ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን እግር ሲጎትት ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ጥሶ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ ከውስጥ ባንዳዎች እና ከውጪ ባእዳን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የጦርነት ጉሰማውን ተያይዞታል፡፡
ኢትዮጵያን በመውጋትና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀው ህገ ወጡ ቡድን፣ ወጣቶችን በማፈስ ትግራይ ውስጥ ወደሚገኙ የወታደራዊ ማጎሪያ ካምፖች እና ወደ ኤርትራ ጭምር እያጓጓዘ ይገኛል፡፡
ግጭት የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና እንደሚጎዳ የሚገባው የመደመር መንግሥት ይህንን ተግባር ልክ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ አሁንም ለትግራይ ህዝብ ሲል በትእግስት እየተመለከተው ይገኛል፡፡
መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ ፈጽሟል፡፡ በዚህም ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ አሳይቷል፡፡
ህገ ወጡ ሕወሓትን ጨምሮ የንግግር ፍላጎት ላላቸው አካላት በሙሉ መንግሥት በሩ ክፍት ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
ይህ የመንግሥት አቋም በተለይ ከሰሜኑ ግጭት ማክተም በኋላ ለሀገራዊ መግባባትና መልሶ ግንባታ ትልቅ መሠረት ሆኗል።
የመደመር መንግሥት ሰላም የኢትዮጵያን አንድነትና የወደፊት ተስፋ ለመቅረጽ መሠረታዊ ምሰሶ እንደሆነ ያምናል፤ ለተግባራዊነቱም እየሰራ ነው፡፡
መንግሥት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖረውም፣ አሁንም የሰላም ጥሪዎችን እያቀረበ ይገኛል፡፡
ይህንን የሚያደርገው መጪው ትውልድ በአሸናፊና በተሸናፊ ትርክት ውስጥ እንዳያድግ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ሀገር ላይ እንዳይደርስ ነው፡፡