የሀገር ውስጥ ዜና

ግብፅንና ሱዳንን ከድርቅ፣ ከጎርፍ፣ ከውኃ ደለልና ከወጪ የታደገው የሕዳሴ ግድብ

By Abiy Getahun

July 23, 2026

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የልማት ምሰሶ ከመሆኑ ባሻገር፣ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ከተፈጥሮ አደጋዎች እየታደጋቸው ይገኛል።

ግድቡ ወቅትን ተከትሎ በዓባይ ወንዝ ላይ ሲከሰት የነበረውን ከፍተኛ የውኃ ፍሰት መዋዠቅ በማስተካከል፣ የቀጣናውን የውኃ ደህንነት በተግባር እያረጋገጠ ያለ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

ቀደም ሲል ዝናብ በሚያጥርበት ወይም ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ይፈጠር ነበር። የሕዳሴው ግድብ ግዙፍ የውኃ ማጠራቀሚያ በመሆኑ ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ቀርፎታል።

ሱዳንም ሆነች ግብፅ ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጥ ውኃ ያገኛሉ፡፡ ግድቡ በክረምት ያከማቸውን ውኃ፣ ዝናብ በሌለበት የበጋ ወቅት ጭምር ስለሚለቅ፣ ሱዳንና ግብፅ ቋሚ የውኃ አቅርቦት እንዲያገኙ አስችሏል።

የውኃው ፍሰት ቋሚ መሆን በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ አርሶ አደሮች በድርቅ ምክንያት ሳይሰጉ ዓመቱን ሙሉ ምርት እንዲያመርቱ ዋስትና ሆኗቸዋል።

በሱዳን የሚገኙ የውኃ ኃይል ማመንጫዎች በበጋ ወቅት የውኃ መጠን በመቀነሱ ምክንያት እንዳይቋረጡ፣ የሕዳሴው ግድብ የሚለቀው ውኃ ቋሚ የኃይል አቅርቦት እንዲኖራቸው አድርጓል።

የዓባይ ወንዝ በየዓመቱ በክረምት ወራት በሚያስከትለው ከፍተኛ ጎርፍ በሱዳን እና በግብፅ ላይ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የቤትና የንብረት መውደም እንዲሁም የእርሻ ማሳዎች መጥለቅለቅ የተለመደ ክስተት ነበር። የግድቡ ተገንብቶ መጠናቅ ይህንን ስጋት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ሱዳን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥፍራዎች ቅርብ በመሆኗ የዓባይ ጎርፍ ቀጥተኛ እና ከባድ ሰለባ ነበረች፡፡

በየዓመቱ በሚከሰት የጎርፍ መጥለቅለቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞቱ ነበር። ለምሳሌ በፈረንጆቹ 2020 በደረሰው ጎርፍ ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ቤት ንብረታቸውን አጥተው ተፈናቅለዋል።

የካርቱም ከተማን ጨምሮ በወንዙ ዳርቻ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ የሸክላና የጡብ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲፈርሱ የነበረ ሲሆን፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ጣቢያዎችም በውኃ ይዋጡ ነበር፡፡

በናይል ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኙ ሰፊ የሰብል ማሳዎች በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ምክንያት ምርት ሙሉ በሙሉ እየወደመ፣ በሱዳን የሚገኙት እንደ ሮሴሬስ እና ሴናር ያሉ ግድቦች ከመጠን በላይ በሚመጣ የውኃ ግፊት የመጣስ ወይም የመደርመስ ከፍተኛ አደጋ ይጋረጥባቸው ነበር፡፡ ግብፅ የአስዋን ከፍተኛ ግድብን በመገንባቷ አብዛኛውን የጎርፍ ማዕበል መቋቋም ትችል የነበረ ቢሆንም፣ ከግድቡ በፊት እና በኋላ የራሷ የሆኑ ከባድ ስጋቶች ነበሯት።

የዓባይ ጎርፍ ከአቅም በላይ በሚሆንበት ጊዜ በአስዋን ግድብ ላይ አደጋ እንዳይፈጥር ሲባል ውኃው ወደ ቶሽካ በረሃ እየተለቀቀ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ያለ ጥቅም በበረሃ እንዲተን ሲደረግ ኖሯል፡፡

ጎርፍ በየዓመቱ ይዞት የሚሄደው ደለል በአስዋን ግድብ እና በናስር ሐይቅ ውስጥ ተከማችቶ የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የግብፅን የረጅም ጊዜ የውኃ ዋስትና አደጋ ላይ ጥሎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በናይል ወንዝ ዴልታ አካባቢ የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች በጎርፍና በደለል ምክንያት እንዳይበላሹ ግብፅ በየዓመቱ ከፍተኛ የመከላከያ ወጪ ታወጣ ነበር፡፡

የሕዳሴ ግድብ ግን ወደ ታችኛው ተፋሰስ የሚለቀቀውን የውኃ መጠን ሳይቀንስ በክረምት የሚከሰተውን ከባድ የጎርፍ ማዕበል እየተከላከለ ይገኛል።

ከኢትዮጵያ ተራሮች በጎርፍ ታጥቦ የሚወርደውን ከፍተኛ የአፈር ደለል በማስቀረት፣ በሱዳንና በግብፅ የሚገኙ ቦዮች እና ግድቦች በደለል እንዳይደፈኑ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሱዳንና ግብፅ በየዓመቱ የቦዮቻቸውን እና የግድቦቻቸውን ደለል ለማጽዳት በአማካይ ለሰው ኃይል እና ለማሽነሪዎች በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጪ ያወጣሉ።

የዓባይ ወንዝ ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ በፊት ከኢትዮጵያ ተራሮች በየዓመቱ ከ157 እስከ 207 ሚሊዮን ቶን የሚገመት ከፍተኛ ደለል ይዞ ይወርድ ነበር። ይህ ደለል በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ወጪ ከፍተኛ ነበር፡፡

የሕዳሴው ግድብ ከመጠናቀቁ በፊት የመጀመሪያዋ የደለል ተጎጂ ሱዳን ነበረች፡፡ ሱዳን በየዓመቱ እንደ ሮሴሬስ እና ሴናር ያሉ ግድቦቿን ተርባይኖች እና የውኃ ማከማቻዎች ከደለል ለማጽዳት ብቻ በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ስታደርግ ኖራለች፡፡

በሱዳን የሚገኙትን ከ10,000 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝሙ ሰፊ የግብርና መስኖ ቦዮችን ከደለል ነጻ ለማድረግ ደግሞ በዓመት እስከ ስድስት ጊዜ ማጽዳት ይጠይቃል። ለዚህም በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ ዶላር ሲፈስስ ቆይቷል፡፡

ግብፅ ከሱዳን ርቃ ብትገኝም፣ ከፍተኛው የደለል ክምችት በግዙፉ የአስዋን ከፍተኛ ግድብ እና በናስር ሐይቅ ላይ ያርፋል።

ደለል በየዓመቱ ግድቡን ስለሚሞላው ግብፅ የውኃ ማከማቻ አቅሟን ለመጠበቅ፣ የመስኖ መውጫ ቦዮችን ለማጽዳት እና የወንዙን ፍሰት የተስተካከለ ለማድረግ በዓመት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ትመድባለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ በመጀመሩ ወደ ታች የሚወርደውን ደለል እስከ 86 – 97 በመቶ ድረስ አስቀርቶ እንደሚያጣራው ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም ሱዳን እና ግብፅ በየዓመቱ ለደለል ማጽጃ ያወጡት የነበረውን ከፍተኛ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማዳን ትልቅ የኢኮኖሚ እፎይታ ሰጥቷቸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ መጀመር የጋራ ተጠቃሚነትን በተግባር ያሳየ ታላቅ ክስተት ነው። ግድቡ የተፈጥሮ አደጋዎችን በማስቀረት ለግብፅና ለሱዳን የህልውና እና የደህንነት ዋስትና በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ይህ ተጨባጭ እውነታ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ እንጂ የጉዳት ምንጭ አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል።