የሀገር ውስጥ ዜና

አንጋፋዋ ድምጻዊት አልማዝ ተፈራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች

By Melaku Gedif

July 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንጋፋዋ ድምጻዊት ሳጅን አልማዝ ተፈራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

ድምጻዊት አልማዝ ተፈራ ባደረባት ሕመም በሕክምና ስትረዳ ቆይታ ነው ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው፡፡

ድምጻዊት አልማዝ በነገሌ ቦረና ተወልዳ ያደገች ሲሆን÷ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በይርጋለም ከተማ የቀለም ትምህርቷን ተከታትላለች።

ከዚያም በጅማ ፖሊስ ኦኬስትራ ባንድ ከምስረታው ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በድምጻዊነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነት እንዲሁም በጃዝ ሙዚቃ ተጫዋችነት አገልግላለች።

ከዚሁ ባንድ ጋርም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዘዋወር የሙዚቃ ሥራዎቿን አቅርባለች።

ድምጻዊቷ ሶስት የሙዚቃ አልበሞችን አሳትማ ለአድማጭ ያደረሰች ሲሆን÷ የመጀመሪያ አልበሟ በ1978 ዓ.ም ለአድማጭ ጆሮ ደርሷል።

በዚህ አልበሟ ላይ ‘ጅማ ላይ ነው ቤቱ’፣ ‘አካል መውደድ’፣ ‘የፍቅር ጽገሬዳ’ እና ሌሎች ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎቿ ተካትተዋል።

አልበሙ ጅማ ከተማ በሚገኝ መንዝ ሙዚቃ ቤት የታተመና ተወዳጅነትን ያተረፈ ነበር። በ1982 ዓ.ም ደግሞ 2ኛ አልበሟን በዚሁ በመንዝ ሙዚቃ ቤት አሳትማ ለአድማጭ አድርሳለች።

ይህ አልበም እንደበኩር ሥራዋ የተደመጠ ባይሆንም የብዙዎችን ጆሮ ያገኘ ስለመሆኑ ድምጻዊቷ በአንድ ወቅት ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች፡፡

በ1993 ዓ.ም ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በፖሊስ ኦኬስትራ ባንድ ውስጥ ማገልገል የቻለችው ድምጻዊቷ÷ በዚህ ወቅትም 3ኛ የሙዚቃ አልበሟን በአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ቤት አሳታሚና አከፋፋይነት ለአድናቂዎችዋ አድርሳለች።

ድምጻዊት አልማዝ ከአልበሞቿ በተጨማሪ በተለያዩ ወቅቶች ተወዳጅ ነጠላ ዜማዎችን ተጫውታለች።

በዜማ እና ግጥም ድርሰት ብቃት ያላት በመሆኗም ብዙዎቹን ሙዚቃዎቿን በእራሷ ዜማ እና ግጥም ደራሲነት አዘጋጅታለች።

በዚህም ከራሷ አልፋ የሒሩት በቀለን ‘እንደ ንጋት ጮራ’፣ ‘የባቄላ አበባ’ እና ‘ቃልኪዳን አክባሪ’ የተሰኙ ዘፈኖችን ግጥምና ዜማ ደርሳለች።

ድምጻዊት፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዋ አርቲስት አልማዝ ተፈራ የሁለት ሴት ልጆች እናት ነበረች።

የአንጋፋዋ ድምጻዊት አልማዝ ተፈራ ቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት በቅዱስ ዮሴፍ መካነ መቃብር ቀን 10 ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቿ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በወርቅአፈራው ያለው