የትግራይ ክልል ህዝብ የህገ ወጡ ሕወሓት የፖለቲካ መያዣ ሆነን አንቀርም እያለ ነው።
ህዝቡ ረጅም ታሪክ፣ ጠንካራ ባህል እና ለኢትዮጵያ አንድነት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ኩሩ ህዝብ ነው።
ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ከ50 ዓመት በላይ፣ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ነግዷል።
ጫካ እያለ “መንግሥት ስሆን ህይወትህን እቀይርልሀለሁ” እያለ ተከታዩን በህልሙ ቅቤ ያጠጣ ነበር።
ስልጣን በያዘባቸውም ጊዜያት ለራሱ እንጂ፣ ለትግራይ ህዝብ ያደረገው አንዳች ነገር የለም።
የትግራይ ህዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ የተለየ ነገር አላገኘም።
ህዝቡ የተረጋጋ ኑሮ መኖርን ይመኝ ነበር።
ህገ ወጡ ቡድን ከማዕከላዊ ስልጣን ከተባረረ በኋላም፣ ጫካ እያለ ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ የትግራይን ህዝብ ለገዛ የፖለቲካ ህልውናው እንደ መያዣ መጠቀሙን ቀጠለ።
ቡድኑ ለፈጸማቸው ህገ ወጥ ድርጊቶች፣ ለሀገር ክህደት ተግባራት እና ለንብረት ዘረፋዎች ከለላ እንዲሆነው የትግራይን ህዝብ “ህልውናህ አደጋ ላይ ነው” በሚል በሀሰት ትርክት በእገታ አቆይቶታል።
በዚህም የህዝቡን አብራክ እየቀማና ለግጭት እየዳረገ፣ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወንድምና እህቶቹ እንዲነጠል ጥረት አድርጓል።
የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ትስስሩ እንዲላላና በሀገሩ ራሱን እንደ ባይተዋር እንዲያይ አድርጎታል።
ቡድኑ ዳዴ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከ50 ዓመት በላይ ትግራይ በህገ ወጡ ጭካኔ ደምታለች።
ወጣቶች ለአላስፈላጊ ጦርነት እንዲማገዱ፣ እናቶች በሀዘን እንዲማቅቁ፣ ህጻናትም ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ አድርጓል።
በቡድኑ ባንዳነት እና በባእዳን ጠላቶች ተላላኪነቱ፣ የትግራይ እናቶች ሳይወዱ ተገድደው ብዙ ልጆቻቸውን ባልተገባ መስዋእትነት አጥተዋል።
ይህ ህዝብን በታጋችነት የመያዝ እኩይ ተግባር ግን አሁን ላይ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ቡድኑ ምንም እንኳን በሃይል የትግራይን ህዝብ አፍኖ ይዞ ቢቆይም፣ አሁን ላይ ግን ነገሮች እየተቀየሩ ነው።
የትግራይ ህዝብ ጦርነት ትርፍ እንደሌለው በደንብ ተረድቷል።
ቡድኑ ከሞት ለመዳን ወጣቶችን እያፈሰ ወደማጎሪያ ይወስዳል፤ እምቢ ያሉትን ይረሽናል። በሌላ በኩል የደቦ ያለህ “ጽምዶ” አትርፈኝ ቢልም፣ ጊዜው በመርፈዱ ማእበል ሊወስደው ደርሷል።
የትግራይ ህዝብ ጥቅሙ እና ደህንነቱ ሊጠበቅ የሚችለውም ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በሰላም፣ በፍትህ እና በእኩልነት ሲኖር ብቻ መሆኑን በሚገባ ያውቃል።
ህዝቡ ቡድኑን ከራሱ ላይ ለማሽቀንጠር አፈሳውንም እምቢኝ እያለ ይገኛል፡፡
እኩይ ዓላማውን ስለተረዳ ወደ ወንድም እህቶቹ ክልሎች እየሄደ ነው።
የህገ ወጡ ቡድን ለ50 ዓመታት ያለማደግና የአዛውንት ህጻንነት፣ የውስጥ ክፍፍል፣ የሙስና እና የስልጣን ጥመኝነት መጋለጥ ህዝቡ በቡድኑ ላይ የነበረውን እምነት ሙሉ በሙሉ እንዲያጣ አድርጎታል።
ህዝቡ አሁን ላይ መብቱን ለማስጠበቅ፣ የራሱን እጣ ፈንታ በራሱ ለመወሰን እና በስሙ የሚነግዱትን አካላት “በቃ!” ለማለት እየተነሳ ይገኛል።
በትግራይ እናቶች ልጆቻችንን ለጦርነት አንሰጥም ሲሉ፣ ወጣቶች የእምቢኝ ጥሪ በራሪ ወረቀቶችን በየከተማው በትነዋል።
በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። የስልጣን ጥመኞቹ ጊዜያዊ አስተዳድሩን አፍርሰው፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በመጣስ ብቻቸውን እየዳሁ ይገኛሉ።
የትግራይ ህዝብ የህገ ወጡ ሕወሓት የግል ንብረት ወይም የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ አይደለም።
የመደመር መንግሥትም የህዝቡን የልብ ፍላጎት እያደመጠ ይገኛል።
ህዝቡ የደረሰበትን ሰፊ ስቃይ እና መከራ ተቋቁሞ፣ አሁን ከተጋረጠበት የአፈና እና የመያዣነት ቀንበር ነጻ የሚወጣበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ህገ ወጡ ሕወሓት ህዝቡን ታጋች አድርጎ የሚቀጥልበት የፖለቲካ ስሌት አክትሟል። የሌላው ክልል ወንድም እህት ለትግራይ ህዝብ አለሁልህ እያለው ነው።
የወደፊቱ የትግራይ መስመር የሰላም፣ የልማት እና ከኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቹ ጋር በጋራ የመበልጸግ መስመር እንጂ የጥፋት ቡድኖች መደበቂያ አይሆንም።