የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ አሻራ ለንብ ሀብት ልማት

By Yonas Getnet

July 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአስርት ዓመታት በፊት ከ40 በመቶ በላይ የነበረው ጠቅላላ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደጊዜ ጥበቃን ካለማግኘት ከ 3 በመቶ በታች አሽቆልቁሎ ነበረ፡፡

ከደን ሽፋን ማሽቆልቆል ጋረ ተያይዞ የውሀ አካላት መቀነስ፤ የአየር ንብረት መዛባት፤ የመሬት ምርታማነት መቀነስ በተለይም ደግሞ የእጽዋት ብዝሀ ህይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፡፡

የእጽዋት ብዝሀ-ህይወት መመናመን በግብርናው ዘርፍ በተለይም በንብ ሀብት ልማት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ፈጥሮ ነበር፤ በዚህም የሀገሪቱ የማር ምርት አመርቂ አልነበረም፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በ2011 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ ንቅናቄው የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር፤ በተከታታይ በተሰሩ ሰፊ ስራዎች የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ይገኛል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም አካባቢዎች የመትከል ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ ስራ ተመናምኖ የነበረውን የኢትዮጵያን የእጽዋት ብዝሀ- ህይወት እንዲያንሰራራ በማድረግ ለግብርና ዘርፉ እድገት አይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ከመጨመር ባለፈ፣ ለንብ ሃብት ልማት ምቹ የሆኑ ምህዳሮችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።

በተለይም ከእጽዋት ብዝሀ- ህይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የንብ ሀብት ልማት፤ መርሀ-ግብሩ ይፋ ከሆነ ጀምሮ በተሰሩ ሰፊ ስራዎች እድገትን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ለንብ ሀብት ልማት ስኬት በቂ አበባ የሚሰጡ ዕፅዋት ምርቱ በሚከናወንበት አካባቢ በቅርበት መኖር አለባቸው።

በዚህ ረገድ በአረንጓዴ አሻራ ወቅት ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚተከሉት የእጽዋት አይነቶች ንቦች ለመቅሰም ተመራጭ የሚያደርጓቸው በመሆናቸውና ረጅም ርቀት ሳይጓዙ በቅርበት እጽዋቱን እንዲያገኙ ስለሚያደርግ የማር ምርትን ያሳድጋል፡፡

በዚህም በንብ ማነብ ወይም በማር ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በማስቻል ላይ ይገኛል፡፡

በመላው ሀገሪቱ በጨመረው የደን ሽፋንና የእጽዋት ብዝሀ-ህይወት ሳቢያ ባደገው የንብ ሀብት ልማት ባገባደድነው በጀት ዓመት ብቻ ከ428 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘርፉ አዳዲስ የስራ እድሎችን በመፍጠር እንዲሁም ከምርቱ በሚገኘው ገቢ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ ማሻሻል አስችሏል፡፡

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በተሰራ ስራ ለንብ ሀብት ልማት ከፍተኛ አቅም የፈጠረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር፤ የተጀመሩ ስራዎች በቁርጠኝነት እያደጉ በመጡ ቁጥር ከማር ምርታማነት ባለፈ በመላው የሀገሪቱ ዘርፎች ላይ ጉልህ እድገት እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

በመልካም ፈቃዱ