የሀገር ውስጥ ዜና

የቴክኖሎጂ ብልጽግና ጉዞ – ዲጂታል ኢትዮጵያ

By Mikias Ayele

July 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምንኖርበት ዘመን ዓለማችን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር አብዮት ውስጥ ትገኛለች።

በዚህ የእድገት ጉዞ ውስጥ የሀገራትን ብልጽግና እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅም መሆኑ ይታመንበታል።

ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በመረዳት፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ከ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025″ ስኬቶች በመነሳት፣ ሀገሪቱን ወደ ቴክኖሎጂ እውቀት የተመራ ኢኮኖሚ የሚያሸጋግር እና በአፍሪካ የዲጂታል መሪ የሚያደርጋትን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን በይፋ ወደ ሥራ አስገብታለች።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ በአሁኑ ወቅት ታላቅ የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ላይ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የዜጎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ በመንግሥትና በዜጎች መካከል ያለውን መተማመን ያጎለብታሉ፤ አገልግሎቶች ዲጂታል መሆናቸው የአሠራር ግልጽነትን በመፍጠር፣ የተጓተተ አሰራርን በማሻሻል እና ሌብነትን በመቀነስ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ያነሳሉ፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ከፍተኛ እድገትን ለማስመዝገብ በምጣኔ ሀብት፣ በመንግሥታዊ አስተዳደር እና በማኅበራዊ ዘርፎች ጉልህ ለውጥ ለማምጣት የነደፈችው የብሔራዊ ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ነው።

ይህ ስትራቴጂ የቀደመው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ዕቅድ የታለመለትን ግብ በከፍተኛ ስኬት ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተጀምሯል።

የዲጂታል ዕውቀትን ማስፋፋት፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥን ማጎልበት እና ተቋማዊ አቅምን በዲጂታል ስርዓት መገንባት ብሎም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ጅማሮዎችን መደገፍ እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎችን ማዘመን ዋና ዓላማዎቹ ናቸው።

ግብርናን ጨምሮ የተለያዩ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆኑ ዘርፎችን በማዘመን በከተማ እና በገጠር መካከል ያለውን የዲጂታላይዜሽን ልዩነት ማጥበብና ሁለንተናዊ እድገትን ለመጎናጸፍ ያስችላል፡፡

የስትራቴጂው ዋነኛ ራዕይ በመላው ሀገሪቱ ያሉ ዜጎች የዲጂታል ስርአትን እኩል የተጠቃሚነት ዕድል እንዲኖራቸው ማስቻል ነው።

ስትራቴጂው ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል። ቴክኖሎጂው በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትሕ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ጥቅም ላይ እንዲውልና የዘርፎቹን ውጤታማነት እንዲያድግ ይደረጋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ የዲጂታል መሠረተ ልማት እና ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት ሥርዓት ይገነባል።

ይህ ሂደት አንድ ሚሊየን አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና የዲጂታል ዘርፉ ለሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የ12 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ አልሟል።

ይህ የሽግግር ሂደት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ የቅንጦት ወይም የሩቅ ምኞት ሳይሆን ሀገሪቷ በራሷ እሴት እና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርታ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተግበር የራሷን የዕድገት ጎዳና በራሷ ለመጥረግ የተለመችው የመበልጸግ ቁርጠኝነት ነው።

የስትራቴጂው ስኬትም ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ የተሸጋገረች እና የኢኮኖሚ እምቅ አቅሟን በተሟላ ሁኔታ የተጠቀመች የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ያደርጋል።

በመልካም ፈቃዱ