አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ከማስቻሉ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፡፡
የክልሉ የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በማጃንግ ዞን በመንገሺ ወረዳ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር ለግብርና ልማቱ ስኬታማነት ልንተጋ ይገባል።
በክልሉ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስራዎች በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች ከማገገማቸው ባለፈ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ገልፀዋል።
በቀጣይም የተጀመረውን ልማት በማሳለጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት ያላሰለሰ ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት እየተከናወነ ላለው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የክልሉ ህዝብ ተሳትፎና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተስፋየ ምሬሳ