የሀገር ውስጥ ዜና

መሶብ ፤ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት

By Mikias Ayele

July 25, 2026

የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ብልሹ አሰራሮች ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ተግዳሮት ናቸው ከሚባሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

መሰል ችግሮችን ለመፍታትም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎች ላይ ቅሬታ የሚፈጥሩ አሰራሮችን ነቅሶ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመደመር መንግሥትም በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡

ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተለያዩ ከተሞች መተግበር የጀመረው የመሶብ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተሟላ ማዕድ የሚወክለው መሶብ አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በማጣመር የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ ርምጃ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት ቀልጣፋ፣ ተዓማኒና ቀጣይነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ማሳያ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ማዕከሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ በመሆኑ ዜጎች የተሳለጠ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው፡፡

የአሰራር ሥርዓቱ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተዳራሽ ማድረግ ያስችላል፡፡

መሶብ ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን የሚያስቀር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ማዕከላቱ እየሰጡት ከሚገኙ ስሉጥ አግልግሎት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

መሶብ አንድ ማዕከል የሕዝብን የአገልግሎት ፍላጎት ያማከለና ሁሉም ዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በአክብሮትና በኃላፊነት መንፈስ የሚገለገሉበት መሆኑ ዘመኑን የዋጀ ያደርገዋል፡፡

በተለይም ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ መስጠቱ ቀደም ሲል ይገጥማቸው የነበረውን እንግልት ለመቅረፍ አስችሏል፡፡

መሶብ ዘመኑን የዋጀና የተለያየ አገልግሎትን በአንድ ጣሪያ ሥር ከመስጠቱ ባለፈ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል አሰራር ያለው መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡

አገልግሎቱ መንግሥት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት ማረጋገጫ ሲሆን ÷ በሀገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጥም እንደ ታሪክ እጥፋት የሚቆጠር ትልቅ ስራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት በዘመናዊ አገልግሎት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የምታከናውነው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

አሁን ላይ በአዲስ አበባ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ፣ ደሴ እና ሌሎች ከተሞች ላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሥራ ጀምረዋል፡፡

በቀጣይም ማዕከሉን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስቀር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡

ለዚህም በትናንትነው ዕለት የኢፌዲሪ መሶብ አገልግሎት ሀገር አቀፍ የመሶብ አገልግሎት የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ አድርጓል፡፡

ስትራቴጂክ እቅዱ የ10 ዓመት እቅድን የመንግሥት የአስተዳደር እና አገልግሎት ፖሊሲን እንዲሁም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ እቅድን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

ይህም የመሶብ አገልግሎት የሚሰጥበት አጠቃላይ ሁኔታ እና የአሰራር ሥርዓት አመላካች ሆኖ እንደሚያገለግል ተመላክቷል፡፡