አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በተገኙበት የወለዱት አራስ እናቶች ጉባኤውን አሳክተው እስኪመለሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ወ/ሮ ሃዳ አልማህዲ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለሀገራዊ ምክክር ከተፎካካሪ ፓርቲ ተወክላ በታላቅ የሀገር ፍቅርና የእኔነት ስሜት ኃላፊነቷን እየተወጣች በነበረበት ወቅት ወንድ ልጅ በሰላም መገላገሏ ይታወሳል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ወ/ሮ ሃዳን በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ማረፍያ ክፍል አዘጋጅተን ለአራስ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አሟልተን እንኳን ደስ አለሽ ብለን ጠይቀናታል ብለዋል።
ወ/ሮ ሃዳ የመጣችበትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እንደምትመለስ ነግራናለች ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ከጋምቤላ ክልል ተወክላ ለምክክር ጉባኤው የመጣችው ወ/ሮ ክርኑዶ ኡጁሉ ወንድ ልጅ በሰላም መገላገሏ የሚታወስ ነው።
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተገኙበት የወለዱት ሁለቱም አራስ እናቶች የመጡበትን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አሳክተው እንዲመለሱ ለምክክሩ በቅርበት በሚመቻቸው ቦታ ማረፍያ መዘጋጀቱን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱም አራስ እናቶች ጉባኤውን አጠናቀው እስኪመለሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን ብለዋል፡፡