የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በአይነቱ ለየት ያለ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየም ልታካሂድ ነው

By amele Demisew

July 26, 2026

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ትኩረት የሚስበውን የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም ታስተናግዳለች አለ መከላከያ ሚኒስቴር።

ከነገ ሐምሌ 20 እስከ 25 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በተገለጸው በዚህ ሲምፖዚየም ላይ 40 ሀገራትና 26 ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አጋሮች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ፓል ፍሪክና ስለ ሁነቱ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ለዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ አስተናጋጅ ሆና መመረጧ በቀጣናው ለሰላም ላበረከተችው አስተዋፅኦ ማሳያ ነው፡፡

በተጨማሪም በመንግሥት የተመዘገበው የልማት ውጤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ እያሳየች ያለው ፈጣን እድገትና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ የፈጠረው ተጽእኖ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ በአፍሪካ የመከላከያ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የጋራ ትብብር የሚያጎለብቱበት መድረክ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ብርጋዲየር ጀነራል ፓል ፍሪክና በበኩላቸው ኮንፍረንሱ በአሜሪካና አፍሪካ መካከል በሎጂስቲክስና በኮሙኒዩኬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት ተሳታፊ ሀገራት የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን አቅሞቻቸውን በመገምገም ክፍተቶችን በጋራ በመለየት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ እንደሚሰሩ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡