አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ የአፍሪካ ጦር ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር.ኤም አንደርሰን አፍሪካ ለዓለም ሰላም፣ ለዓለም ደኅንነት እና ለዓለም መረጋጋት አሁንም ወሳኝ ስፍራ ትይዛለች አሉ።
የ2026 የአፍሪካ ኮሙኒኬሽንና ሎጂስቲክስ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ሲምፖዚየሙ ከ40 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎችንና 26 ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አጋሮችን በማሳተፍ በሎጂስቲክስ፣ በመገናኛ ቴክኖሎጂና በደኅንነት ዘርፎች የጋራ ትብብርን ለማሳደግ ያለመ ነው።
ጀኔራል ዳግቪን አንደርሰን በመድረኩ እንዳሉት፤ በአፍሪካ የሚታዩ የሽብርተኝነት፣ በኦንላይን የሚፈጸም የመረጃ ምዝበራ፣ ህገወጥ የሰዎች እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ስጋቶችን መከላከል ትብብር ይጠይቃሉ።
ከትብብር ባለፈ ጠንካራ የሎጂስቲክስና የመገናኛ አቅም እንደሚፈልግ ጠቅሰው፤ የዘመናዊ ወታደራዊ ብቃት መሠረቱ መሣሪያ ሳይሆን አቅምን ማጎልበት ማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል።
የትኛውንም ዘመናዊ መሣሪያ ብትገዙም፣ ማስቀጠልና ወደ ተልዕኮ ስፍራ ማድረስ ካልቻላችሁ ፋይዳ የለውም ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተለይም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች፣ ድሮኖች፣ ሳተላይቶችና ዘመናዊ የመገናኛ ሥርዓቶች የጦርነትን ባህሪ እየቀየሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአፍሪካ ሀገራት እነዚህን ለመጠቀም አቅማቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደ ስኬታማ ምሳሌ በማንሳት፣ ድርጅቱ ዛሬ የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ሊሆን የቻለው አውሮፕላኖችን በመግዛት ብቻ ሳይሆን የጥገናና የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማትን ቀድሞ በመገንባቱ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሳፍንት ብርሌ