ፋና ስብስብ

ደማቅ ስኬት የተመዘገበበት የቱሪዝም ዘርፍ

By Yonas Getnet

July 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት በትኩረት ባከናወናቸው ተግባራት አስደናቂ ለውጥ ከተመዘገበባቸው በርካታ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሽ ነው፡፡

የመደመር መንግሥት በሚከተለው የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ከአምስቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎች ቱሪዝምን አንዱ አምድ አድርጎ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

ዘርፉ በፖሊሲ የተደገፈ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፥ እንደ ሀገር በርካታ አዳዲስና ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችንና መሰረተ ልማቶችን መገንባት ተችሏል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተተገበሩት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ አግዘዋል።

በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ በመዲናዋ የተመዘገበውን አስደናቂ እድገት እንደ ሀገር በማስፋት በገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ዓይን ገላጭ ስራዎች ተሰርተዋል።

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡

በዚህ ረገድ በጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ፣ ኮይሻ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ሸበሌ እና ሌሎች ስፍራዎች የተገነቡትን መዳረሻዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንዲሁም ከዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ ስሟን የሚመጥን ውበትና ገፅታ አንድትላበስ ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ከመጨመሩ ባሻገር ለነዋሪዎችም ለጎብኚዎችም ምቹ እንድትሆን አስችሏል፡፡

የእንጦጦ፣ የወዳጅነት እና የአንድነት ፓርኮች፣ የወንዝ ዳርቻ እና የከተማ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች የመዲናዋን የቱሪዝም ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻሉ ቁልፍ የልማት ስራዎች ናቸው።

አዲስ አበባ በርካታ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ የሚያስችላት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕመርታ ያሳየችበት የቱሪዝም ዘርፍ መሆን ችሏል፡፡

እንደ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የመሳሰሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች መገንባት ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ግዙፍ  አቅምና ውበት ፈጥረውላታል፡፡

ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በየዓመቱ በርካታ ሚሊየን ዓለም አቀፍ ተጓዦች የሚሸጋገሩበት ቁልፍ ማዕከል በመሆኑ ተጓዦች በአደስ አበባ እና አካባቢዋ የሚገኙትን መስህቦች እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የስቶፕኦቭር ጉብኝት በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል፡፡

በዘርፉ በተከናወኑ ፈረጀ ብዙ ስራዎች በ2018 ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን በመሳብ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በድህረ ኮቪድ-19 በፍጥነት ካገገሙ ሀገራት መካከል የምትጠቀስ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

ከመዳረሻ ልማትና አይነተ ብዙ መስህቦች ባለቤት ከመሆናችን በተጨማሪ የቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻልና የሀገራችን ምልክት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት ከ145 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች መብረር ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የመደመር መንግሥት የምድረ ቀደምትነታችን ማህተም የሆኑ ቅርሶችን ጨምሮ የበርካታ ባህልና ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ካሏት ነባር መዳረሻዎች በተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማትና ቅርሶቻችን የሚመጥኑ ሙዚየሞችን በመገንባት ውብ ገፅታ እንዲላበሱ አድርጓል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ተዘርፈው ወደ ውጭ የሄዱ ቅርሶች በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ማግባባት እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

እንደ የፋሲል ግንብ፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥትና ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን የመሳሰሉ ታሪካዊ ቅርሶች በጥናት ላይ የተደገፈ ዕድሳት ተደርጎላቸው ለዕይታ ክፍት ሆነዋል፡፡

ማህበረሰቡን በቱሪዝም ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰጠው ትኩረት በገበታ ፕሮጀክቶች በተገነቡ ሪዞርቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

ከዚህም ባሻገር የአካባቢው ነዋሪዎች ለጎብኚዎች የሚቀርቡ የእደ ጥበብ ምርቶችን የሚሸጡበት የገበያ ዕድል ተፍጥሮላቸዋል፡፡

የመደመር መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ በመዳረሻ ልማት፣ በቅርስ ዕድሳትና ማስመለስ፣ በአገልግሎት አቅርቦት፣ በቪዛ ማሻሻያና በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ አብነት የሚሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል።

በውጤቱም የጎብኚዎችን ቁጥር ጨምሯል፤ የቱሪዝም ገቢ ከፍ እንዲልና የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ገፅታ እንዲሻሻል ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ