የሀገር ውስጥ ዜና

የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል – አቶ አህመድ ሺዴ

By Mikias Ayele

July 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የ2018 የበጀት ዓመት አፈጻጸም እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት አካሂደዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በመድረኩ እንዳሉት፤ የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው አፈጻጸም እጅግ ውጤታማ ነው።

ይህ ጠንካራ አፈጻጸም በተለይም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግና ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረጉ ትብብሮችን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ያነሱት።

በተጨማሪም በ2018 በጀት ዓመት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ አካላት ጋር በተደረገው የብድር ዕዳ ሽግሽግ ስምምነት መሰረት የዕዳ መክፈል የተጀመረበት ውጤታማ ዓመት እንደነበር ጠቁመዋል።

የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን በጀት ውጤታማ በሆነ መንገድ ስራ ላይ ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ፈቃዱ ሆረታ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እና የተቋሙን ዓላማ የሚያሳኩ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ከማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ጎን ለጎን የተጀመሩ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጣቸው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡