የሀገር ውስጥ ዜና

የገጠር ኮሪደር የከተማና ገጠርን ሁለንተናዊ ትስስርን ለማሳለጥ

By Melaku Gedif

July 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማት ከተሞች ዘመኑን የዋጁ፣ ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሁም ለቀልጣፋና ዲጂታል አገልግሎት ምቹ ይሆኑ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

በመደመር መንግሥት እሳቤ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ አሁን ላይ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በተመሳሳይ በገጠር አካባቢ የሚኖር የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እየተከናወነ የሚገኘው የገጠር ሞዴል መንደር ሥራም አበረታች ነው፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የኑሮ መሰረቱ በገጠር አካባቢዎች ነው፡፡ የገጠር ኮሪደር ልማትም በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ዘዬ ለማሻሻልና ወደ ዘመናዊነት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

መርሐ ግብሩ ለማሕበረሰቡ ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓትን የሚያላብስ፣ ውብና ጽዱ የመኖሪያ አካባቢ ውስጥ የመኖር ዕድልን የሚፈጠር ከመሆኑ ባሻገር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ሚናው ትልቅ ነው፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማት የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘዬ በማሻሻል፣ የአርሶ አደሩን ጤና በመጠበቅ እንዲሁም ዘመናዊነትን በማንጸባረቅ ከተሜነትን ወደ ገጠር ያመጣል።

በገጠር ኮሪደር የሚሰሩ ሞዴል መንደሮች በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ በመሆናቸው አርሶ አደሩ በቀላሉ በመተግበር ጤናማ እና ክብር ያለውን ሕይወት እንዲኖር ያስችላሉ፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማት በከተማ እና ገጠር መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትስስር በማሳለጥ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ተጠቃሚነትን ያጠናክራል፡፡

በውጤት ደረጃ የሕብረተሰብ ሽግግርን የሚያመጣ ሲሆን÷ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥር እና የአርሶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት የሚቀይር ነው የገጠር ኮሪደር ሥራ፡፡

የገጠር ኮሪደር የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በመቀነስ የተመጣጠነ ዕድገትን ከማምጣት ረገደም ጉልህ ሚና አለው፡፡ አርሶ አደሩ ዘመኑን የዋጀ አሰራር እንዲከተል በማድረግ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፤ ጓሮውን በዶሮ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት እንዲያለማም እድል ይሰጣል፡፡

የገጠር ኮሪደር የሶላር ኃይልን ያካተተ በመሆኑ ኢትዮጵያ ያሰበችውን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በተግባር የሚያረጋግጥና ማሕበረሰቡ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር በቀላሉ ትስስር እንዲፈጥር ያስችላል፡፡

የገጠር ሞዴል መንደሮች ግንባታ ቀላል ወጪ የሚጠይቅ እና በአካባቢ ከሚገኙ ግብዓቶች የሚከናወን መሆኑ ሥራውን ይበልጥ የተሳለጠ ያደርገዋል፡፡

አሁን ላይ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ በተለያዩ ክልሎች እየተተገበረ ሲሆን ÷ ተዳራሽነቱን ለማጠናከርም የሚመለከታቸው አካላት በትብብርና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፡፡