ጤና

የቻይና አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ያጠናክራል – ፕሬዚዳንት ታዬ

By Yonas Getnet

July 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት ትብብር ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።

የቻይና-አፍሪካ የሮቦቲክ ቀዶ ሕክምና እና የኢንዶስኮፒክ ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የቻይና አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት የትብብር ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን የቆየና የጠነከረ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።

በሕክምናው ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው÷ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች የዜጎችን የጤና ውጤቶች በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያን የጤና ሪፎርም አጀንዳ በስኬት ወደፊት ለማስቀጠል በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሪፎርም አጀንዳው ውስጥ የጤና የሰው ኃይል ልማትን ማፋጠን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አንስተው ÷ ተመርቀው ሥራ የጀመሩት የማሰልጠኛ ማዕከላት ለቀጣዩ ትውልድ የኢትዮጵያ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ዋና ማፍሪያ ሆነው ያገለግላሉ ብለዋል።

ተቋማቱ ለጠቅላላው የአፍሪካ አህጉር የእውቀት እና የላቀ አገልግሎት ማዕከል ሆነው እንደሚያገለግሉ ነው ያስረዱት፡፡

በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለው ሁለገብ ትብብር በሁሉም ዘርፎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ናቸው።

ቻይና እና ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ጠንካራና አርአያነት ያለው ትብብር መገንባታቸውን ገልጸው÷ በቀጣይም በጤናው ዘርፍ የሰው ኃይል ልማትንና አቅምን በመገንባት ረገድ የሚደረገው የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ተቋማዊ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።