አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የበጎ ፈቃድና የልማት ሥራዎችን በጥብቅ ቅንጅት መምራት ይገባል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባ አዳነች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የቤት ግንባታና የማህበራዊ ድጋፍ ሥራዎችን አፈጻጸም ከከተማዋ አመራሮች ጋር ገምግመዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክረምት ወቅት ለሕብረተሰቡ ዘላቂ ጠቀሜታ የሚሰጡ የበጎ ፈቃድና የልማት ሥራዎች በስፋት እየተተገበሩ ነው፡፡
በክፍለ ከተሞችና በተቋማት መካከል የአፈጻጸም ልዩነቶች በመኖራቸው ቀጣይ ሥራዎች በጥብቅ ቅንጅት ሊመሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የቤት ግንባታን ማፋጠን፣ የፍሳሽ ማለፊያ ዲችዎችን ማጽዳትና አዳዲስ ግንባታዎችን ማካሄድ እንዲሁም ከፍተኛ ሃብት ወጥቶባቸው የለሙ ሥፍራዎችን አሰራርና ጽዳት በአግባቡ መጠበቅ ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በግንባታ ምክንያት በሚወጡ ተረፈ ምርቶች መንገዶችን የሚያበላሹ እና ዲችዎችን የሚዘጉ አካላት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲያርሙና ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላ ከዕቅድ በላይ እንዲከናወንና ለአስፈላጊው ጥራት ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትንና የከተማ ጽዳትን የሕብረተሰቡ ባሕል የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወንም ነው የጠቆሙት።
የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚሰጠው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትና የጎልማሶች ትምህርት በልዩ ትኩረት እንደሚመሩም ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ከተረጂነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ሰብዓዊ ሥራዎችን ለማጠናከር የተገነቡ መጋዘኖች በቂ የድጋፍ ቁሳቁስ እንዲኖራቸው ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡