የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር በር ለጠንካራ ብሔራዊ ደህንነት

By Mikias Ayele

July 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ታሪክ ኃያላን የነበሩና አሁንም ኃያልነታቸውን አስጠብቀው የሚገኙ ሀገራት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ጠንካራ የባሕር ኃይል እና የወደብ ባለቤቶች ናቸው፡፡

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያወሱት ኢትዮጵያም ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ በነበሯት ሀገረ መንግሥታት እንደ አዱሊስ ያሉ የዓለም አቀፍ ንግድና የቀጣናዊ ተጽእኖ መሰረት የነበሩ ወደቦች ባለቤት ነበረች፡፡

በዚህም በዘመኑ በዓለም ላይ ከነበሩ ጠንካራና ኃያል ሀገራት በግንባር ቀደምትነት ትነሳ ነበር።

በቅርብ ጊዜያትም በአሰብና ምጽዋ ወደቦች ጠንካራ የባሕር ኃይልና የንግድ ወደቦች የነበሯት ሲሆን በቀጣናው ፖለቲካና ደህንነት ላይም ወሳኝ የሆነ ተሰሚነትና ተጽእኖ ነበራት፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን እና የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚስማሙት፤ ቀጥተኛ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለአንድ ሀገር የጂኦፖለቲካ ተፅዕኖ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የመከላከያ ጥንካሬ በአጠቃላይ የሉዓላዊነት እና የህልውና ጉዳይ ነው።

የባሕር በር መኖር ሀገርን ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተጽእኖ፤ ከትራንዚት ወጪ ጫና እና ከውጭ ወታደራዊ ስጋቶች በመጠበቅ ረገድ የሚኖረው ሚና አጠያያቂ አይደለም፡፡

የባሕር በር ያለው ሀገር ጠንካራ የባሕር ኃይል በመገንባት የውሃ ክልሉን ብሎም ቀጣናውን ከአደጋና ከህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መጠበቅ ይችላል፤ ይህም ሊሰነዘሩ የሚችሉ ወታደራዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ስለሚያስችል የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት የተጠበቀ ያደርጋል፡፡

የባሕር ላይ ውንብድና፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውሮች እና ንግዶች አብዛኛውን ጊዜ የሚካሄዱት በባሕር መስመሮች ላይ እንደመሆኑ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ጥበቃ በማድረግ ይህንን ዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋት መከላከል ያስችላል፡፡

አንድ የባሕር በር የሌለው ሀገር የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ከውጭ በሚያስገባበት ወቅት በሌላ ሀገር ወደብ በኩል ስለሚያልፍ የሀገር ምስጢርና ብሔራዊ ደህንነቱን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገር ወታደራዊ አቅምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ይደቅናል፡፡

የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የዓለም የንግድ መስመሮችንና ወሳኝ የባሕር ቀጣናዎችን ስለሚጋሩ በዓለም አቀፍም ሆነ በቀጣናዊ የፖለቲካ መድረኮች ላይ ከፍተኛ የመደራደር አቅምና ተጽዕኖ አላቸው።

የባሕር በር መኖር ሀገርን ከውጭ ወታደራዊ ስጋት፣ ከንግድ ተጽእኖ እና ከጎረቤቶች ዲፕሎማሲያዊ  ጫና የሚጠብቅ ዘላቂ የደህንነት ጋሻ ነው።

ስለዚህም የባሕር በር ባለቤትነት ለአንድ ሀገር የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ ምሰሶ ነው።

በአጠቃላይ የባሕር በር ለአንድ ሀገር የንግድ መውጫ መስመር ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነት፣ የፖለቲካ ነፃነት፤ የሉዓላዊነት እና የህልውና መሰረት ነው።

ከላይ እንደተነሳው የኢትዮጵያም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተራ የባሕር መውጫ ፍለጋ ሳይሆን ራስን የመከላከል፤ የሀገራዊ ደህንነትን የማረጋገጥ፤ የፖለቲካ ነጻነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ፤ በጠቅላላው የህልውና ጥያቄ ነው፡፡

ይህም በመሆኑ የመደመር መንግሥት የባሕር በር ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ይህንን እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

በመልካም ፈቃዱ