አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚሼል ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትብብር የሚያሳድጉ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መስኮችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚና መዋቅራዊ ማሻሻያ የተመዘገቡ ቁልፍ ስኬቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ሀገራዊ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ እና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፥ መንግሥት በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር፣ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማሻሻልና ለውጭ አልሚዎች አማራጮችን ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ማርክ ሚሼል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስመገበቻቸውን ውጤቶች እንዲሁም መንግሥት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሻሻል እያከናወናቸው ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የሀገራቱን የሁለትዮሽ የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ አጋርነት እንዲሁም የንግድ ተቋማትን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ የገንዘብ ተቋማት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክትን ለመደገፍ ባላቸው ፍላጎት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ማስፋት የሚያስችሉ ውይይቶችን ለማድረግ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ