አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መሰረተ ቢስ ክሶችን ከማሰማት ይልቅ በጋራ ማዕቀፎች ተስማምታ መደራደር ያዋጣታል አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፡፡
ሚኒስትሩ ግብጽ የምታቀርባቸውን የሀሰት ውንጀላዎች አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፥ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን የጋራ ሀብት የሆነው የሕዳሴ ግድብ ከዓድዋ ድል በመቀጠል የአንድነትና የትብብር ማሳያ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
አፍሪካውያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ደስተኞች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን ግብጽ የግድቡ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በርካታ ክሶችን ስታቅርብ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያለማንም ርዳታ በራሳቸው ገንዘብና ጉልበት የገነቡትን ግድብ ግብጽ ያለበቂ ምክንያት እንደ ስጋት መቁጠሯ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለግብጽ እና ለተፋሰሱ ሀገራት ስጋት ሳይሆን በረከት መሆኑን ጠቁመው፥ ግድቡ በግብጽ እና ሱዳን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ያስቀረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ግድቡ ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፥ ለአብነትም ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ከግድቡ የአሌክትሪክ ኃይል በመግዛት ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ግብጽ ኢትዮጵያ በያዘችው ውሃ ምክንያት የግድቦቿ የውሃ መጠን እንደቀነሰ አድርጋ ክስ ማቅረቧ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርና የጋራ እድገት መርህን እንደምትከተል የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ግብጽ ተጨባጭ ያልሆኑ ክሶችን ከማቅረብ ይልቅ በትብብር መንፈስ በጋራ ማዕቀፎች ተስማምታ መደራደር ያዋጣታል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማትና የመጠቀም መብት ያላት ሉዓላዊ ሀገር በመሆኗ ከብልጽግና ጉዞዋ በተቃራኒ ለቆሙ ኃይሎች ቦታ የላትም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ