የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሀብት ለጋራ ጥቅም ለማዋል በትብብር መስራት እንደሚገባ ቁልፍ መልዕክት አስተላልፋለች

By Hailemaryam Tegegn

July 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ያላትን ሀብት ለጋራ ጥቅም ለማዋል በትብብር መስራት እንደሚገባ ኢትዮጵያ ቁልፍ መልዕክት አስተላልፋለች አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፡፡

49ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት፥ ስብሰባው በህብረቱ በጀት፣ በፋይናንስ ራስን መቻል፣ በመዋቅራዊ ሪፎርምና በሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ህብረቱ በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም በፋይናንስ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም መሆን እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ህብረቱ በራሱ አቅም የሚመራና የአህጉሪቱን የልማት አጀንዳዎች በውጤታማነት የሚያስፈጽም እንዲሆን አባል ሀገራት የህብረቱን በጀት በራሳቸው አቅም የመሸፈን ቁርጠኝነት ሊያሳዩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል ነው ያሌት፡፡

አፍሪካ በሰላምና ደህንነት፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት በርካታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በመድረኩ ላይ የአፍሪካን ሀብት ለጋራ ጥቅም ለማዋል በትብብር መስራት እንደሚገባ ቁልፍ መልዕክት አስተላልፋለች ብለዋል፡፡

በስብሰባው በበጀት፣ በፋይናንስ ራስን መቻልና በመዋቅራዊ ሪፎርም ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች የህብረቱን አቅም የሚያጠናክሩ ዘላቂ የፋይናንስ መሰረት የሚፈጥሩ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

አጀንዳ 2063 የአፍሪካ ህብረት የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ሲሆን፥ የሰላምና ደህንነት፣ የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች አህጉራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮችን ያካተተ ነው ብለዋል።

የልማት አጀንዳዎቹና የአፈጻጸም ሂደታቸው በአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች እየተገመገሙ የመጨረሻ ውሳኔዎች እንደሚሰጥባቸው ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ ሙሉ ነጻነቷን ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ ነጻነት እውን መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፥ ለዚህም አባል ሀገራቱ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡