የሀገር ውስጥ ዜና

በህዝባዊው አረንጓዴ አሻራ ዘንድሮ ከ8.5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ይተከላሉ

By Melaku Gedif

July 29, 2026

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ሃይል ልማት በስፋት እየሰራች ሲሆን፣ በዚህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም እየሆነች ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሀገራት ለአየር ብክለት ምንም አይነት ድርሻ ባይኖራቸውም፣ ተጎጂነቱን ግን ካደጉት ሀገራት እኩል ይጋራሉ፡፡

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት ይነገራል፡፡ በወቅቱ በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም የደን ሽፋናችን ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መደህየት እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተጀመረ፡፡

ከዚያን አመት ጀምሮ ህዝባዊ ንቅናቄ በመሆን በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በሁሉም የሃገራችን አካባቢዎች የመትከልና የመንከባከብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዓመት በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

በ2012 ዓ.ም 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን፣ በ2014 ዓ፣ም 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ 2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 8 ቢሊዮን ችግኝ የተተከለ ሲሆን በ2018 ዓ.ም ዘንድሮ ደግሞ 8.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአንደኛው እና በሁለተኛው ምዕራፍ የተተከሉ ችግኞችን 50 ቢሊዮን ለማድርስ ግብ የታጣለ ሲሆን፣ ይህም ተግባር ሀገራችን በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሃ-ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

የፕሮግራሙ ውጤታማነት እና ስኬት የተገኘው ሥራውን ሀገር አቀፍ በማድረግ፣ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ በማሳተፍ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ካለው ሀገራዊ የልማት ፋይዳ ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት፣ አድናቆት እና ምስጋና ያገኘ ሲሆን ሌሎች ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት ፕሮግራሙን በሞዴልነት መከተል ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየአመቱ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን እንዲጋሩ እያደረገች ነው፡፡