አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በአዲስ አበባ፣ በመቐለ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ማዕከላት በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቆይታ እንዳሉት፤ አሁን ላይ የፌዴራል መንግሥት ያደረገውን ርብርብ ተከትሎ ተማሪዎቹ ወደ ፈተና አዳራሾች ገብተዋል።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የፈተናው መጀመር በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲቃና እና ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
ለፈተናው ስኬት አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማከናወን ተማሪዎቹ ያለምንም እንግልትና ስጋት ፈተናቸውን እንዲወስዱ የጸጥታና የትምህርት ባለሙያዎች የተቀናጀ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል ተብሏል።
በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መርሐ ግብር 30 ሺህ የሚጠጉ የክልሉ ተማሪዎች በአዲስ አበባ፣ በመቐለ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በወረቀትና በበይነመረብ ፈተናውን እንደሚወስዱ ተመላክቷል።
በሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ጥፋት ሳቢያ ትምህርታቸው ተቋርጦ የቆዩ የክልሉ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናቸውን በተለያዩ ማዕከላት እየወሰዱ መሆኑ ተገልጿል።
ትውልዱን በጦርነት ግንባር መማገድ የማንነቱ መገለጫ የሆነው ሕገወጡ ቡድን በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ሰቆቃና ስጋት አጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ይህ የፈተና መርሐ ግብር መከናወኑ የቡድኑን ጸረ-ሕዝብ አካሄድ በግልጽ ያሳያል።
በቡድኑ አሻጥርና ጸረ-ሰላም ተግባራት ለከፍተኛ መስተጓጎልና የሥነ-ልቦና ጫና ተጋልጠው ለነበሩት ተማሪዎች የመደመር መንግሥት ባደረገው ድጋፍና ቀጣይነት ያለው ክትትል ወደ ፈተና እንዲገቡ መደረጉ ትውልዱን ለመታደግ ያለውን ዓላማ በግልጽ ያሳየ ነው።
በግዛቸው ግርማዬ