አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዘንድሮው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀዋል አለ ግብርና ሚኒስቴር፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ይመር ዳውድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
የፊታችን ሰኞ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በመላው ኢትዮጵያ ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኞች በ291 ሺህ 617 ሔክታር መሬት ላይ የሚተከሉ ሲሆን÷ ለዚህም 10 ሺህ 941 ቦታዎች ተለይተዋል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል በአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ ከ476 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ችግኞች የሚተከሉባቸው 191 ሺህ 290 ሔክታር የሚሸፍኑ 4 ሺህ 801 ቦታዎች ተለይተዋል ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ከ308 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ችግኞች የሚተከሉባቸው 68 ሺህ 872 ሔክታር የሚሸፍኑ 3 ሺህ 538 ቦታዎች መለየታቸውን አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ9 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በ2 ሺህ 910 ሔክታር ላይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ41 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በ16 ሺህ 861 ሔክታር ላይ፣ በሲዳማ ክልል ከ10 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በ2 ሺህ ሔክታር ላይ እና በሶማሌ ክልል ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በ1 ሺህ 67 ሄክታር ላይ ለመትከል ታቅዷል፡፡፡
በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ10 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ችግኞች፣ በሐረሪ ክልል 300 ሺህ ችግኞች፣ በትግራይ ክልል ከ535 ሺህ በላይ ችግኞች፣ በአፋር ክልል ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ችግኞች፣ በጋምቤላ ክልል ከ287 ሺህ በላይ ችግኞች፣ በአዲስ አበባ ከ1 ሚሊየን በላይ እና በድሬዳዋ ከ213 ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የችግኝ መትከያ ጉድጓድ፣ ለችግኝ መትከያ በተለዩ ቦታዎች ጂኦሪፈረንስ እንዲሁም ችግኞችን ወደ ሚተከሉበት አካባቢ ማድረስና ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ለሕብረተሰቡ አስፈላጊው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አቶ ይመር በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ የተያዘውን እቅድ በስኬት ለማከናወን የፊታችን ሰኞ መላው ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ዐሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ