የሀገር ውስጥ ዜና

የብዝኀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ግንባታ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማሳካትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ጠንካራ መሠረት ጥሏል

By Abiy Getahun

July 30, 2026

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የመደመር ዕሳቤን መሠረት ያደረጉ በርካታ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ ተግብሯል።

በተለይም በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መሠረት በመለወጥ፣ አጠቃላይ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የብዝኀ ዘርፍ የልማት ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በግብርናው ዘርፍ የነበረውን ባሕላዊ አሠራር በመቀነስና አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል። ሀገሪቱ ቀደም ሲል ለስንዴ ፍጆታ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትልቅ ውጤት አምጥቷል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት ከመሸፈን አልፋ ምርቱን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ጀምራለች። በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በፕሮቲን የበለጸገ ምግብ ለማቅረብ የተጀመረው ንቅናቄ የእንቁላል፣ የወተትና የስጋ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።

በመደመር ዕሳቤ ሥር የቱሪዝም ዘርፍን የኢኮኖሚው አዲስ ሞተር ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች የሀገሪቱን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በአዲስ አበባ የተገነቡት እንደ አንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች እንዲሁም በክልሎች የተገነቡት የወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ እና የታሪክ ጸጋ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ አዳዲስ መስህቦች ሆነዋል።

የመደመር መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማነቃቃትና የዲጂታል ሥርዓት ዝርጋታ ላይ በትኩረት ሰርቷል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በማጠናከር፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የተደረገው ጥረት የዘርፉን ዕድገት አፋጥኗል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር የቴሌኮም ዘርፉን ለግል ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ፣ የቴሌብር እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን በማስፋፋት የገንዘብ ዝውውርንና የንግድ አሠራርን ዘመናዊና ቀልጣፋ አድርገውታል።

ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የተወሰዱት የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ አቅም ገንብተዋል። የመደመርና የሕዝባዊ አንድነት ትልቅ ማሳያ የሆነው ሕዳሴ ግድብ፣ የኃይል ማመንጨት ሥራዎችን በይፋ በመጀመር ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ኤክስፖርት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መሠረት ጥሏል። የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ማሻሻያን ጨምሮ የተወሰዱት ደፋር የፖሊሲ እርምጃዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የንግድ ምህዳሩን ለማስተካከል ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።

በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት የተከተለው የብዝኀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ኢኮኖሚው በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይደገፍ በተመጣጣኝ ሁኔታ እንዲያድግ አድርጓል። እነዚህ የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።