የሀገር ውስጥ ዜና

የስልታዊ ቡድን ምክክር ዛሬም ቀጥሎ ውሏል

By abel neway

July 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው 250 አባላት ባሉት 16 ስልታዊ ቡድኖች የተደራጁ ተመካካሪዎች ምክክር በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ ውሏል፡፡

በ250 አባላት የተደራጁ 16 ስልታዊ ቡድኖች ከጥቃቅንና ንዑስ ቡድኖች በተገኙና በተጠናቀሩ የአጀንዳ ምክረ ሃሳቦች ላይ ከትላንት ጀምረው ተመካክረዋል፡፡

ትላንት በነበረው የምክክር ውሎ ከእያንዳንዱ ስልታዊ ቡድን በተመረጡ 25 የአጀንዳ ምክረ ሃሳብ አጠናካሪዎች አማካኝነነት የተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦችን ያዳመጠው 16ቱ ባለ 250 አባላት ስልታዊ ቡድን አባላት በጥቃቅንና በንዑስ ቡድኖች ተነስተው በቀረበው ቃለ ጉባዔ ላይ ያልተካተቱና በአግባቡ ያልተብራሩ ያላቸውን ሃሳቦች ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

ስልታዊ ቡድኖቹ በዛሬው ውሏቸው የተሰጡ አስተያየቶች ተካትተውበት በድጋሚ የተደራጀውን ቃለ ጉባዔ የጋራ በማድረግ በቀጣይ ለሚደረገው እና 500 ተመካካሪዎችን ለያዙ 8 ቡድኖች ምክክር ዝግጅት ሲያደርጉ ውለዋል፡፡

በነገው ዕለት በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ የክልል (ከተማ መስተዳደር) እና የፌዴራል ተወካዮች ምርጫ የሚደረግ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!