የሀገር ውስጥ ዜና

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን በእመርታ ለማስቀጠል ይሰራል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

By amele Demisew

July 30, 2026

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን በእመርታ ለማስቀጥል በትኩረት ይሰራል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳሉት ÷ የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ስብሰባውን አካሂዷል።

በዚህም ምክር ቤቱ በዓመቱ ውስጥ እንዲፈፀሙ ያስቀመጣቸውን ተግባራት አፈፃፀም በጥልቀት በማየት አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

ም/ቤቱ አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የስራ ክንውን፣ የዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ሒደት እንዲሁም ‘የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስ’ ኢኒሼቲቭ ትግበራ አፈጻጸም ገምግሞ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ የሚገኙ አዳዲስ የዲጂታል ሥራዎች ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጋር ያላቸውን ተጣጣሚነት መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችን በእመርታ የሚያድግበት ዘመን ላይ ነው፤ ም/ቤቱም ለዚሁ ዕድገት ተገቢውን ሚና ለመወጣት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡