ፋና ስብስብ

ተስፋን እንትከል

By Abiy Getahun

July 31, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተመናምኖ የነበረውን የደን ሽፋን እንዲያገግም በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ከመታገል ባሻገር የምግብ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ ተስፋ ተጥሎበት እየተተገበረ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና አስተባባሪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው መርሐ ግብሩ፤ በየዓመቱ በተከናወኑ የችግኝ ተከላ ስራዎች፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል በሚያበረክተው አስተዋጽኦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን በማትረፍ ላይ ይገኛል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ‘ተስፋን እንትከል’ በሚል መሪ ቃል በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም የተጀመሩትን የሀገሪቱን ስነ-ምህዳር መንከባከቢያ ተግባራት ማጠናከርና ለትውልድ የሚተርፍ ዘላቂ ልማትን መፍጠር ነው።

ዘንድሮም ይህንን ታሪካዊ ተግባር አጠናክሮ ለመከወን ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡

በሀገሪቱ እስካሁን በተከናወኑት መርሐ ግብሮች ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የዘንድሮው ዓመት ሀገሪቱ ልታሳካው ካለመችው 65 ቢሊየን ችግኞች ግብ ላይ ለመድረስ ትልቅ መንደርደሪያ ነው።

መላውን ኢትዮጵያዊ በማንቀሳቀስ በአንድ ጀምበር ብቻ 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ታላቅ ሀገራዊ እቅድ ተይዞም ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ሶስት ቀናት ብቻ ቀርተዋል።

በዚህ ታሪካዊ ኩነት ላይ ለመሳተፍም፤ ዕለቱ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

በመርሐ ግብሩ ሊተከሉ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና አፕል ያሉ ለምግብነትና ለገበያ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት ተዘጋጅተዋል።

ይህም ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባለፈ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን መርሐ ግብሩ በ2011 ዓ.ም ሲጀመር ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተጠናክሮ መቀጠል የደን ሽፋንን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ዘንድሮ የሚተከለው ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኝ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ተግባር ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ተፈጥሮ በማከም ምርታማነትን በማሳደግ ከዕርዳታ ጥገኝነት ወጥታ ራስን ወደ መቻል የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት የሚለካው ችግኞችን በመትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብና የጽድቀት ምጣኔን በማሳደግ ጭምር በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ዜጋ የዚህ ታላቅ ትልም ባለቤት በመሆን ዐሻራውን ማኖርና የተፈጥሮ ሀብቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማውረስ ይኖርበታል።

በመልካም ፈቃዱ