አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ፕራምፕ በጋዛ ውስጥ ሰላምን ለማምጣት ሀማስ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ለመፍታት ተስማምቷል አሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በጋዛ የሰላም ቦርድ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሀማስ ትጥቁን ለመፍታት መስማማቱን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ጋዛን በአዲስ የፍልስጤም መንግስት ለማስተዳደር ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን መግለጫ ተከትሎ ሀማስ በጋዛ የሰላም እቅድ መስማማቱንና ይፋዊ መግለጫ እንደሚያወጣ ስማቸው ያልተጠቀሰ የታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ ባለስልጣን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እስራኤል ግን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ይፋዊ አስተያየት አለመስጠቷን የጠቀሰው ዘገባው፥ የስምምነቱ አካል መሆን ካልፈለገች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቅር እንደሚሰኙ ገልጿል፡፡
ሀማስ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታ ሲናገር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለ ሲሆን፥ ይህም በሰላም ድርድሩ ውስጥ ትልቁ ተጠባቂ ነጥብ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ባለፈው መስከረም ወር በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው ባለ 20 ነጥብ የጋዛ የሰላም ስምምነት እቅድ የምዕራፍ አንድ ድርድር ሳይተገበር መቅረቱ ይታወሳል፡፡
ዋና ዓላማው ጋዛን ከሽብር የጸዳ አካባቢ ማድረግ ነው በተባለለት በዚህ የሰላም ዕቅድ፥ ከሀማስ ትጥቅ መፍታት በተጨማሪ በቀጣይ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ለቆ እንዲወጣ የሚያስገድድ ሀሳብ መካተቱ ነው የተገለጸው፡፡
በእመቤት ሲሳይ