የሀገር ውስጥ ዜና

ዝንጀሮ የሚሞተው በወጣትነቱ የዘለለውን ገደል በእርጅናው ለመዝለል ሲሞክር ነው

By Hailemaryam Tegegn

July 31, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የህገ ወጡ ቡድን አመራሮች የመድረኮች የቀደመ የተራ ሽፍትነት ባህርያቸውን እየገለጡ ነው፡፡ከውጪ ታሪካዊ ጠላቶች እና ከዓለም አቀፉ የአሸባሪ ቡድን አልሻባብ ጋርም ጥምረት በመፍጠር የኢትዮጵያን ህዝብ ለመውጋት እየተዘጋጁ እንዳለ ከራሳቸው አንደበት ሰምተናል፡፡ለህገ ወጡ ቡድን ሀገርን ክዶ ከባዕዳን ጋር መሰለፍ አዲስ አይደለም፡፡በደርግ ወቅት ከሶማሊያው ሰይድ ባሬ ጋር በማበር በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍልየተፈጸመውን ወረራ መደገፉን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ቡድኑ አሁን ላይ በግብፅ የእጅ አዙር መሪነት እና በሻእቢያ ተባባሪነት ጽምዶን ተገን አድርጎ ለመንቀሳቀስ እየሞከረ እንዳለ መሪዎቹ ሰሞኑን በተገኙባቸው መድረኮች ገልጸዋል፡፡ለቡድኑ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ጥቅም ማስቀደም ልማዱ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ከውጭ ኃይሎች ጋር ባደረገው ጥምረት ኤርትራ ስትገነጠል ሆን ብሎ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ አድርጓታል፡፡ ይህ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡በባዕዳን ሴራና በቡድኑ ተላላኪነት በህዝብ አንጡራ ኃብትና ላብ የተገነባው የሕዳሴ ግድብ እንዲበላሽ፣ ፕሮጀክቱ እንዲጓተት እና እንዲቆምም ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡የቡድኑ ክፋት መረን የለሽ ቢሆንም፣ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል እና ሉዓላዊነት ሀገር ወዳድ ህዝብ መሆኑን ሲያስመሰክር የኖረ ህዝብ ነው።ከቀሪው የኢትዮጵያ ወንድም እና እህቶቹ ጋር በሰላም፣ በፍቅር እና በአንድነት የመኖር ጽኑ ፍላጎትም አለው።በትግራይ ምድር የተመዘገቡ የዓድዋ፣ የዶጋሊ እና የጉንደት ታሪካዊ ድሎችን፣ የጠላት ወረራዎችን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በማሸነፍ የጋራ መስዋዕትነት ያስመዘገበ ኩሩ ህዝብ ነው፡፡ህዝቡ ካሳለፋቸው የዘመናት የጦርነት ጠባሳዎች በመነሳት፣ ዛሬ ከሁሉም ነገር በላይ የሚሻው ዘላቂ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ልማትን ነው።የመደመር መንግሥትም የትግራይን ህዝብ የሰላም ወዳድነት ስለሚያውቅ፣ የሰሜ ጦርነት እንዳይከሰት፣ ከተፈጠረም በኋላ ጦርነቱን በአሸናፊነት ቢደመድምም ለትግራይ ህዝብ ሲል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከተሸናፊው ቡድን ጋር ቁጭ ብሎ በመፈረም ሰላም እንዲወርድ አድርጓል፡፡በዚያኑ ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ንጹሐን ዜጎች የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያገኙ መንግሥት የአየርና የየብስ ትራንስፖርቶችን ክፍት አድርጓል።በጦርነቱ የወደሙ የኃይል፣ የኮሙኒኬሽንና የባንክ አገልግሎቶችን ለመመለስ ሰፊ በጀትና የሰው ኃይል መድቦ ይህንንም አሳክቷል፡፡

ነገር ግን ቡድኑ ብዙም ሳይቆይ ሰላም ያወረደውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ እንዳይተገበር አደናቅፏል፡፡አበው “ዝንጀሮ የሚሞተው በወጣትነቱ የዘለለውን ገደል በእርጅናው ለመዝለል ሲሞክር ነው” እንደሚሉት ሁሉ፣ ቡድኑ አቅመ ቢስነቱን አልተረዳም፡፡ በስተሽምግልናው ከዘራ ተደግፎም ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፡፡ለ50 ዓመታት የነበረው የስልጣን ጥመኝነት ያልተላቀቀው ህገ ወጡ ቡድን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን አፍርሶ ክልሉን ብቻዬን ካላስተዳደርኩ በሚል እየተንጠራወዘ ይገኛል፡፡በዚህ ሁሉ አጋጣሚ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቢቆይም የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ወደ አንድነትን፣ አብሮነትን እና የጋራ ብልፅግና ለማምጣት በሆደ ሰፊነት ሲመለከተው ቆይቷል፡፡ለዘላቂ ሰላም መውረድና ለሕዝቡ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ ሲልም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ማቅረቡና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ አይዘነጋም።ሆኖም ግን፣ በአሁኑ ወቅት የሕግ የበላይነትን በመጣስና የትግራይን ሕዝብ የሰላም ፍላጎት ወደ ጎን በመተው፣ ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ዳግም ለተራ ሽፍትነት በክልሉ ሕዝብ ላይ አደጋ እየደቀነ ይገኛል፡፡የመደመር መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የሰላም ጥሪዎች፣ በጦርነትና በግጭት የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ ሕይወት ለመታደግ ያለውን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል።ይህ ሁሉ ጥረት የሚደረገው የትግራይ እናትና ልጅ ዳግም የጦርነት ሰለባ እንዳይሆኑና በሰላም ወጥተው መግባት እንዲችሉ ነው።መንግሥት የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካልና የሉዓላዊነቱ መገለጫ መሆኑን በጽኑ ያምናል።ለሕዝቡ ሲልም ተደጋጋሚ የሰላም በሮችን ከፍቷል፡፡ ሕገ ወጡ ቡድን ግን አሁኑም የጦርነት ከበሮ ከመደለቅ አልተቆጠበም።ቡድኑ የትግራይን ወጣት በማስገደድ እያፈሰ ለዳግም እልቂት እያዘጋጀ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡በክልሉ የሚገኙ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ሳይቀር በግዳጅና በማስፈራራት ወደ ካምፖች እያጋዘ መሆኑን አይተናል፡፡በቁጥጥሩ ሥር ባሉ የመገናኛ ብዙኃኖች አማካኝነት ሕዝቡን ከሌላው የኢትዮጵያ ወንድም እህቶቹ ጋር የሚያጋጩ የጥላቻ ትረካዎችንና የጦርነት ፕሮፓጋንዳዎችን በስፋት እየረጨ ይገኛል።ለሕዝቡ የሚላከውን የምግብና የነዳጅ እርዳታ ለታጣቂዎቹና ለጦርነት ዝግጅቱ ፍጆታ እያዋለው መሆኑ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል።ይህ አካሄድ ቡድኑ ከጦርነትና ከቀውስ ውጭ መኖር እንደማይችልና የትግራይን ሕዝብ እንደ መያዣና የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረጉን የቀጠለበት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።የትግራይ ሕዝብም የቡድኑን የጥፋት አጀንዳ በመረዳት፣ የራሱንና የልጆቹን መጻኢ ዕድል ከቡድኑ የጥፋት መንገድ ማዳን ይኖርበታል።