አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቦች በብዙ መልኩ የተጋመዱ፣ የተዋለዱና በጋራ የኖሩ ናቸው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸው እንዳብራሩት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በዘመናት መካከል አብረው ሲኖሩ በብዙ መልኩ የተጋመዱ፣ የተሳሰሩ፣ የተጋቡ፣ የተዋለዱና በጋራ የኖሩ ናቸው።
በተለይ ደግሞ አማራና ኦሮሞ በአቀማመጣቸውና በቁጥራቸው ከፍ ስለሚሉ በኢትዮጵያ ታሪክ መለስ ብለን እያንዳንዱን ታሪክ ብንመዝን በሶስት ዋና ዋና መንገዶች የተጋመዱ መሆናቸውን እናያለን ብለዋል።
አንደኛው መጋመድ በጋብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግለሰቦች ሲንቀሳቀሱ የመዛመድ ልምምዳቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ፖለቲካዊ ጋብቻ መሆኑን በማንሳት፤ በታሪክ ውስጥ በፖለቲካው ወንበር ለማጽናት በሚደረግ ጥረት ሰፋፊ ፖለቲካዊ ጋብቻዎች መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።
ሶስተኛው ደግሞ ባህላዊው ጉዲፈቻ እንደሆነ ገልጸው፤ ብዙዎች በነገስታት ደረጃ የምናያቸውም ጭምር በዚህም በዚያም ወገን በጉዲፈቻ ምክንያት ሰፊ መስተጋብሮች፣ አብሮ ማደጎች ባህል መጋራቶች በኦሮሞም በአማራም ህዝቦች መካከል የቆየ ልምምድ ነው ብለዋል።
ጥቂት ምዕተ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያን ታሪክ ብንመለከት የሸዋ ሱልጣኔቶች የሚባለው ዘመን 350 ዓመት ገደማ ቆይቷል በማለት ገልጸዋል።
የሸዋ ሱልጣኔቶች መንግሥት በፈጠሩበት ከባቢ ላይ በስፋት ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ አርጎባዎች፣ ጉራጌዎች፣ ሌሎችም ብሔሮች ያሉባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሱልጣኔቶቹ ቆይታ ጊዜ ውስጥ ብዙ መጋመድ እንደነበረ መገመት ይቻላል ነው ያሉት።
ከ130 ዓመት በላይ የቆየውና ከሸዋ እስከ ዘይላ የሚዘረጋው የኢፋት ሱልጣኔትም በቆይታው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መስተጋብር መፍጠሩን በአብነት አንስተዋል።