አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ ውል እድሳት እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተራዝሟል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ አስታውቆት የነበረውን የቤት ኪራይ ውል እድሳት ነው እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ያራዘመው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመግታት የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎ በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ ተከራይ የውል እድሳት ምዝገባ ጊዜ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የነበረው እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን ቢሮው አስታውቋል። የውል እድሳት ጊዜው በሕብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት የተራዘመ ሲሆን ÷ ይህም ነዋሪው ያለምንም መጨናነቅ እንዲዋዋል ያስችላል፡፡ ነዋሪው በሁሉም ክ/ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት ፤ በየወረዳው በተዘጋጁ የውል ቦታዎች እና በሁሉም ክ/ከተማ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስፈላጊውን መረጃ በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል መገለጹን የቢሮው መረጃ አመልክቷል፡፡