አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ም/ቤት እያካሄደ በሚገኘው 12ኛ መደበኛ ጉባዔ በ2019 በጀት ዓመት የክልሉን የልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ በጀት 402 ቢሊየን 285 ሚሊዮን 713 ሺህ 544 ብር አድርጎ አጽድቋል። የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀቱ በ2018 በጀት ዓመት ከተመደበው የ78 ነጥብ 4 በመቶ ወይም የ176 ቢሊየን 831 ሚሊየን 934 ሺህ 307 ብር ዕድገት እንዳለው የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ አታላይ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡ ከዓመታዊ በጀቱ 71 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው በክልሉ ከሚሠበሠብ ገቢ፣ 27 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው ከፌዴራል መንግሥት ጥቅል የቀመር መደበኛ ድጋፍ ድርሻ እንዲሁም ቀሪው ደግሞ ከልዩ ልዩ ምንጮች እንደሚሸፈን ተመላክቷል፡፡ የተመደበው በጀት በዓመቱ ለዘላቂ ልማት ዕቅድ ማስፈጸሚያ፣ ለልዩ ልዩ ሪፎርሞች እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች፣ ለድህነት ተኮር ሥራዎች እና የክልሉን የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ሥራ ላይ ላዋለው ከ39 ነጥብ 1ቢሊየን ብር በላይ የተጨማሪ በጀት ማጽደቁን አሚኮ ዘግቧል፡፡