የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማህበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ

By Mikias Ayele

August 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማህበረሰቡ እንደተለመደው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ለመርሐ ግብሩ የሚሆኑ የቦታ ልየታ፣ የጉድጓድ፣ የችግኝ አቅርቦት እና ሌሎች አስፈላጊ የዝግጀት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በነገው ዕለት በሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን የችግኝ ተከላ ሀገራዊ ንቅናቄ የክልሉ ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት ዐሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ንቅናቄ በኦሮሚያ ክልል 191 ሺህ 290 ሄክታር ስፋት ያላቸው 4 ሺህ 801 ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ 476 ሚሊየን 693 ሺህ 506 ችግኝ ተዘጋጅቷል።