አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ክረምት ከሰኔ ማግስት እስከ መስከረም ማብቂያ ድረስ ምድርን የሚያርስ፣ የጎሰቆለው እና ግጦሽ ያገረጣው ጋራ እና ሸንተረር በአረንጓዴ ካባ የሚሸፍን እና ሕይወትን አዲስ መልክ የሚሰጥ የተፈጥሮ ድንቅ ስጦታ ይታይበታል።
ይህ የዝናብ ወቅት አርሶ አደር ይቅር እና ወፍ የዘራው ሁሉ ሕይወት የሚዘራበት ወቅት ነው፡፡
ከኢትዮጵያውያን ጥንታዊ የተፈጥሮ ጥበቃ ፍልስፍና እና የችግኝ ተከላ ባህል ጋር በስውር ክር የተሳሰረው የኢትዮጵያ ክረምት ተፈጥሮ በቸርነቷ የምታዘንበውን የውሃ በረከት ተጠቅሞ ማህበረሰቡ የምድርን ልምላሜ ለመመለስ ክንዱን ያነሳል፤ በዚህም የሰው ልጅ ጥረት ከተፈጥሮ ዑደት ጋር ተስማምቶ የሚፈስበት ታላቅ ሀገራዊ እውነት ይገለጣል።
በኢትዮጵያ ተማሪዎች ክረምቱን ዛፍ ለመትከል ያስባሉ በበጋው እምብዛም ባይንከባከቧቸው እንኳን ለዛ የሚሆናቸውን ስንቅ እጽዋቱ ከክረምቱ ስራቸውን ወደ ምድር ጥልቅ ሰደዉ እንዲቋጥሩ አስቀድመው መትከል ተለምዷል።
ምድሪቱ በዝናብ ስትረሰርስ ዓመቱን ሙሉ ደረቅ የነበሩ ጅረቶች ዉሃ ያዝላሉ እንኳንስ ታስቦ ጉድጓድ ተቆፍሮ የተተከለ ችግኝ ይቅርና መሬት ላይ በስህተት ያረፈ ፍሬን ጨምሮ ምንም የማይለመልም ነገር የለም፡፡
እንደምን ያለ ነው የወገቧ መቅጠን አያበቅለው የለም ክረምት እና ማህፀን፤
ተብሎም ተገጥሟል እውነት ነው ክረምት የማያለመልመው እና የማያፀድቀው ነገር የለም፤ ማህፀንም አያፈራው ውበት የለም፡፡
ኢትዮጵያም ለዚህ ይመስላል የአረንጓዴ ዐሻራ ስራዋን ለማከናወን ይህን ወቅት የመረጠችው፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ችግኝ መትከልና አካባቢን መንከባከብ ከማህበረሰቡ ስነ-ልቦና፣ እምነትና ባህላዊ እሴቶች ጋር የተቆራኘ የትውልዶች ቅርስ ነው።
እንደ ዋንዛ፣ ጽድ፣ ዝግባ፣ ወይራና ኮሶ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎችን ለጥላ፣ ለአፈር ጥበቃ፣ ለውሃ ምንጮች ህልውና እና ለባህላዊ መድሃኒቶችን ለማዘጋጀት የመጠቀም ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ሀገር በቀል እውቀት አላቸው።
ይህ የኖረና የደረጀ የችግኝ ተከላ ባህል በዘመናችን ወደተቀጣጠለው “የአረንጓዴ ዐሻራ” ንቅናቄ በመሸጋገር ህጻን አዋቂ ሳይል በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአንድነት የሚተሙበትና ዐሻራቸውን የሚያሳርፉበት ሀገራዊ ንቅናቄ ሆኗል።
ንቅናቄው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የአፈር መሸርሸርን ለመግታትና የከርሰ ምድር ውሃን ለመጨመር፣ የደን ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ከዚህም ባሻገር እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ማካተቱ የአካባቢ ጥበቃውን ከምግብ ዋስትና እና ከኑሮ መሻሻል ጋር አስተሳስሮታል።
ኢትዮጵያም ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅታለች።
ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ‹‹ተስፋን እንትከል›› በሚል መሪ ቃል የክረምቱ ተፈጥሯዊ ጸጋ ከኢትዮጵያውያን የጋራ የስራ ባህል ጋር ተዋህዶ የነገዋን ሀገር በልምላሜ ለመገንባት የሚያስችል የማይናወጥ መሰረት ጥሏል።
በእመቤት ሲሳይ