የሀገር ውስጥ ዜና

የተፈጥሮ ሚዛኑ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለትውልድ የማውረስ ጥረታችን ሊጠናከር ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ

By Hailemaryam Tegegn

August 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ በንቃት በመሳተፍ የተፈጥሮ ሚዛኑ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለትውልድ ለማውረስ ጥረታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል አሉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በነገው ዕለት የሚካሄደውን የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኅብረት ተስፋን በመትከል ታሪክ ማስመዝገብ አለብን ብለዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ለህልውና መሠረት የሆነውን ብዝሃ ህይወት ከመጥፋት ለመታደግና እንደ ውሀና አፈር ያሉ መተኪያ የሌላቸው የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሀገራዊ መርሐ ግብር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመግራት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረት የሚጥል ይጥላል ነው ያሉት፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆነ ሥነ ምኅዳር የሚበዛበት መሆኑን ገልጸው፥ መርሐ ግብሩ ይህንን የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን በዘላቂነት ከመግታት ባሻገር ተራሮቻችንን ወደ ሀብት ምንጭነት ማሻገር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮ የአንድ ጀንበር ተከላ የክልሉ ሕዝብ ነገ ከማለዳው ጀምሮ በየአካባቢው በተዘጋጁ የተከላ ቦታዎች በመገኘት በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ንቅናቄ 16 ሺህ 861 ሄክታር መሬት ስፋት ያላቸው 1 ሺህ 345 ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ 41 ሚሊየን 324 ሺህ 212 ችግኝ ተዘጋጅቷል።