የሀገር ውስጥ ዜና

በወሊሶ ከተማ በ470 ሚሊየን ብር የተገነባው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተመረቀ

By Hailemaryam Tegegn

August 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማ በ470 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

ፕሮጀክቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ክልልና ከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን በዋን ዋሽ ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መገንባቱ ነው የተገለጸው፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ዘጠኝ አዳዲስ የከርሰ ምድር ውሃ ምንጮችንና 5 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችል ግዙፍ የውሃ ማጠራቀሚያ ይዟል።

በተጨማሪም 77 የዋና እና የስርጭት መስመር አቅርቦት ያለው ፕሮጀክቱ፥ በወሊሶ ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ከ156 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ የከተማውን ዕድገት ታሳቢ ያደረገና በነዋሪዎች የሚነሱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ የክልሉ መንግሥት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ በክልሉ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች መሰል የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሥራዎችና ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል፡፡

በጎህ ንጉሱ