አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከ800 ሺህ በላይ ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል አለ በአስተዳደሩ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን።
በባለስልጣኑ የደን ልማት ዳይሬክተር ማስረሻ ይመር እንዳሉት፥ በነገው ዕለት ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ በአስተዳደሩ በተመረጡ ውሃ ገብ በሆኑ አራት ቦታዎችና ህብረተሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች እንደሚተከሉ አስረድተዋል።
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸው፥ ችግኞቹ ወደሚተከሉበት ስፍራ ተጓጉዘዋል ብለዋል።
በነገው ዕለት በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ75 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ነው ያሉት።
በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ5 ሚሊየን በላይ ለደን ልማት፣ ለጥላና ለውበት እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ችግኞች እየተተከሉ እንደሆነ አመልክተዋል።
በተሾመ ኃይሉ