የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ ያስተሳሰረ የጋራ ንቅናቄ ነው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ

By tigist gizachew

August 03, 2026

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ሕዝቦች ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ የሚያቆምና የሚያስተሳስር ሀገራዊ ንቅናቄ ነው አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፡፡

አፈ ጉባዔ አገኘሁ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የአንድ ጀንበር የ800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡

አፈ ጉባዔው በዚህ ወቅት ÷ አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

ችግኝ መትከል ብቻ የመጨረሻ ስኬት እንዳልሆነ ጠቁመው ÷ ከተከላ በኋላ ችግኞቹን በአግባቡ መንከባከብ፣ መጠበቅና ለፍሬ ማብቃት ለመርሐ ግብሩ ዘላቂ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የትብብር፣ የመደመርና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከር ኢትዮጵያውያን ለአንድ የጋራ ዓላማ የሚሰባሰቡበት ጠንካራ መድረክ መሆኑን አውስተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ የደን ሽፋንን በማስፋት፣ የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና የአካባቢ ሚዛንን በማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል።