አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ።
ርዕሰ መስተዳደሯ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ዐሻራቸውን ባኖሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሀገሪቱ የተራቆቱ መሬቶችን ወደ አረንጓዴ ሽፋን በመቀየር የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ እና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ውጤታማ አፈጻጸም እያስመዘገበ ነው።
መርሐ ግብሩ ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል የሚካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ከደን ዛፎች ባሻገር ለምግብና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚያገለግሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እፅዋትን በስፋት ማካተት እንደሚገባ አመልክተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰው÷ ዘንድሮ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ዘመቻ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮ 16 ሚሊየን 180 ሺህ ችግኞችን በመትከል 9 ሺህ 452 ሄክታር መሬት ለመሸፈን መታቀዱን አንስተው፤ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዘመቻ ደግሞ 330 ሄክታር መሬት ላይ 6 ነጥብ 42 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
ይህም መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የአፈር ለምነትን እንዲያድግ፣ የውሃ ሀብት እንዲጠበቅ እንዲሁም የግብርና ምርታማነትን እንዲጎለብት በማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የፍቅር፣ የአንድነትና የሁለንተናዊ ብልጽግና ተስፋን የሚያጎለብት በመሆኑ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ዜጎችና ባለድርሻ አካላት በንቃት ተሳትፈው ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት