አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአየር ንብረት መፍትሄ የምታቀርብ ሀገር በመሆን እውቅና አግኝታለች አሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍረስ ወርቁ (ዶ/ር)።
አደፍረስ ወርቁ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በመሬት ማገገምና በማህበረሰብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረ ስትራቴጂያዊ መርሃ ግብር ነው።
መርሐ ግብሩ ከፌዴራል እስከ መንደር ድረስ በመንግሥትና በማህበረሰብ የተቀናጀ ተሳትፎ እየተተገበረ መሆኑን አንስተው፤ ሁሉም ዜጎች በቀጥታ በመሳተፍ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በዚህም በሕብረተሰብ ተሳፎ አሁን ላይ በብሔራዊ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
የተጀመረው የተከላ መርሐ ግብር የብሔራዊ አንድነትና የልማት ተሳትፎ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ችግኞች በ2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸውን ገልጸው፤ የተከሉት ችግኞች ከ80 በመቶ በላይ የጽድቀት መጠን እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተጎዱ መሬቶችን በማገገም፣ የደረቁ ምንጮችን በመመለስና የደን ሀብትን በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን አመልክተዋል።
የሀገሪቱ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን አስታውሰው፤ በዓመት 92 ሺህ ሄክታር የነበረው የደን ጭፍጨፋ ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማለቱ የመርሐ ግብሩ ዋነኛ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያስገኘው መርሐ ግብሩ፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ አረንጓዴ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸው፣ የፍራፍሬ ምርት መስፋፋቱና የአርሶ አደሮች ምርታማነት መጨመሩ ተጨባጭ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍም በተጎዱ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሮች ላይ የማገገም ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸው፤ የጠፉ የውሃ ምንጮችና ሐይቆች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እየተመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጥረቶች ተግባራዊ ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአየር ንብረት መፍትሄ የምታቀርብ ሀገር በመሆን እውቅና እያገኘች መምጣቷን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-32) በማስተናገድ የአረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ የሀገሪቱን የአየር ንብረት መፍትሄዎች ለዓለም ተሞክሮዋን እንደምታጋር አብራርተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለተፈጥሮ ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለሥራ ፈጠራና ለሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ገጽታ መጠናከር ያለውን አስተዋጽኦ በማስቀጠል ቀሪዎቹን ችግኞች በመትከል የዘንድሮው ብሔራዊ ዕቅድ እንዲሳካ ሁሉም ዜጎች በተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት