አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ በአንድ ቀን 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያ ክብረወሰን የሰበረችበት እና ማድረግ መቻሏን ደጋግማ ያሳየችበት ዕለት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀምበር የግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት÷ በዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 26 ሚሊየን ዜጎች በበጎ ፈቃድ በመሳተፍ ለትውልድ ተስፋ የሚጥል ታሪካዊ ተግባር አከናውነዋል።
ይህም ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ማሳካት የሚችሉትን ለዓለም በተግባር ያሳየ ክንውን መሆኑን ጠቅሰው 26 ሚሊየን ዜጎች ያለ ክፍያ እና በአብዛኛው በዝናብ ውስጥ ሙሉ ቀን በመስራት ያሳዩት ተሳትፎ በቀላሉ ሊደገም የማይችል ብሔራዊ አቅምና አንድነት ማሳያ ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው የብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ዜጎች በአንድነት ለሀገራቸው ያሳዩት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ተስፋና ሞራል የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጅማሬ አንስቶ እስካሁን 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው ቀሪው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ በቀሪዎቹ ወራት እንደሚተከል አስረድተዋል።
ይህም የመርሐ ግብሩን አጠቃላይ ዓመታዊ ግብ ለማሳካት ጠንካራ መሠረት የጣለ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ያላትን የአፈጻጸም አቅም ዳግም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ችግኝ በማዘጋጀት፣ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በጂኦ-ሎኬሽን ቴክኒካል ድጋፍ፣ በመረጃ ሪፖርት እና በተከላ ሥራ ለተሳተፉ ሁሉም ዜጎች ከልብ የመነጨ ምስጋናም አቅርበዋል።
በቀጣይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በተመሳሳይ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ቅንጅትና ቁርጠኝነት በማስቀጠል የበለፀገ፣ አረንጓዴና ዘላቂ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ወገኖች በአንድነት እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት