የሀገር ውስጥ ዜና

ግብርናው የኢኮኖሚውን መዋቅር ለመቀየር ያለው አቅም ከፍተኛ መሆኑን ያረጋገጠ ተግባር

By Abiy Getahun

August 04, 2026

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለረጅም ዓመታት የስንዴ ፍላጎቷን ለማሟላት በውጭ ሀገር ምርት እና በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ ነበረች።

ለዚህም በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኩንታሎችን ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ታሪክ በመቀየር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የተረፈ ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የሚያስችል ትልቅ መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመረችው ስትራቴጂካዊ ጉዞ ውጤት ማሳየት ጀምሯል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የኩታ ገጠም እርሻ እና የምርታማነት ማደግ ዋና ዋና መንስኤዎቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት መደበኛውን የዝናብ ወራት ብቻ ከመጠበቅ ወጥቶ፣ በበጋ ወቅት በመስኖ በመጠቀም ሰፊ መሬት ማልማት ችሏል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ትርፋማ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች ምርታማ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡

በኩታ ገጠም እርሻ አነስተኛ አራሽ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በአንድ ላይ በማስተሳሰር በቴክኖሎጂ እና በትራክተር የታገዘ ምርት እንዲያመርቱ ሆኗል።

የተሻሻሉ የስንዴ ዘሮችንና ማዳበሪያን በስፋት በመጠቀም በሄክታር የሚገኘውን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል።

ይህ ምርታማነት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ በመተካት ትርፍ ምርትን ወደ ክልላዊና ዓለም አቀፍ ገበያ ማስገባት እንዲቻል በር እየከፈተ ነው፡፡

ቀደም ሲል ለስንዴ ግዢ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረትም፣ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተጀምሯል።

ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ስንዴ በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካን የምግብ ዋስትና የማገዝ ተስፋዋን አጠናክራለች።

በመደመር መንግሥት ጥቂት ዓመታት ብቻ በዘርፉ በተሰሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አንዷ ትልቋ የስንዴ አምራች ሀገር መሆን ችላለች።

የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት፣ ራስን ከመመገብና ትርፋማ አምራች ከመሆን አልፎ፣ ወደ ውጪ ላኪነት ያሸጋገራት ቁርጠኛ ተግባር ሆኗል፡፡

ይህ ከላኪነት ጋር የተያያዘው ስኬት የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ለመቀየር ያለው አቅም ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል።