አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመቋቋም ባለፈ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ነው፡፡
ይህ መርሐ ግብር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ ከባቢን በመፍጠር የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የሚቆጠር በረከት እያተረፈችበት የሚገኘው መርሐ ግብሩ የመንግሥትና የሕዝብ ቅንጅት በላቀ ደረጃ እንዲታይ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ እውቅናዎችን እንድታገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡
የደን ውድመትን በመከላከልና የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የደን ሽፋን እንዲጨምር ያስቻለ ሲሆን፥ በረሃማነትን መከላከል፣ የድርቅ አደጋን መቀነስና መሬትን ከመራቆት መታደግን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ዓላማን የሰነቀ ነው፡፡
በችግኝ ጣቢያና በጥብቅ ሥፍራዎች በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የምግብ ዋስትና መሰረት ሆኖ ከማገልገል ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ ለኢትዮጵያ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኘ ነው፡፡
በትናንትናው ዕለት በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መላው ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት ሌላ አዲስ ታሪክ ጽፈዋል፡፡
ይህም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ጥብቅ ቅንጅት ለመላው ዓለም ገልጦ አሳይቷል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ