አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ግንባታ ሂደት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚለወጠው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ዕቅድና የሕዝብ ተሳትፎ ለአንድ ዓላማ ሲሰናሰል ነው፡፡
የትናንቱ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ የተሳካው የመንግሥትና የሕዝብን ለሀገራዊ ውጥን የመናበብን አቅም በተግባር ገልጦ አሳይቷል፡፡
805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ቀን መትከል ትልቅ ክብረወሰን ነው፤ ከቁጥርም ባሻገር ለሀገር ግንባታ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ታሪካዊ ሁነት ነው፡፡
የሀገር ግንባታ መንግሥት በሚያስቀምጣቸው ሀገራዊ ግቦችና በሚያመላክታቸው አቅጣጫዎች መሰረት ቢጀመርም፤ የሚሳካው ግን በእውነተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ነው።
በዚህ ሂደት መንግሥትና ሕዝብ ተለያይተው ከመቆም ይልቅ አንድ ሀገራዊ ግብን የሚያሳኩ ተናባቢ ኃይሎች ይሆናሉ።
የአረንጓዴ ዐሻራ ከችግኝ ተከላ ባሻገር የመንግሥት ዕቅድ የሕዝብ ንቁ ተሳትፎን ሲያገኝ የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ማሻገር እንደሚችሉ ሁነኛ ማሳያ ሆኗል፡፡
ሀገር ግንባታ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ በአንድነት የሚቆም ማህበረሰብን መፍጠር፣ በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ የሚሻገር ከባቢን ማረጋገጥና ለጠንካራ ኢኮኖሚ መሰረት የሚሆን ዘላቂ የሀብት ምንጭ መፍጠርን ያካትታል።
በዚህ ረገድ አረንጓዴ ዐሻራ የሕዝብ ትስስር የታየበት፣ አካባቢን የሚጠብቅና ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ለሀገር ግንባታ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡
ችግኝ መትከል በራሱ የአካባቢ ጥበቃ ተግባር ቢሆንም፤ ሚሊየኖች በአንድ ዓላማ በባለቤትነት ስሜት ሲሳተፉበት የጠንካራ ሀገር ግንባታ ሂደትን ያሳልጣል።
የሀገር ግንባታ ረጅም ጉዞ ነው፤ በዚህ ጉዞ ዕቅድና ተግባር፣ መንግሥትና ሕዝብ ተናብበው ሲጓዙ ርዕዩ ይሰምራል፤ ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ትጸናለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ዐሻራ አካል ነው፡፡
ሕዝቡ በግድቡና በአረንጓዴ ዐሻራ ያሳየውን ከፍተኛ ተሳትፎና ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ የመቆም ቁርጠኝነት በሌሎች የዘላቂ ሰላምና ልማት ተግባራት ላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ኪዳን ያሰረበት ጭምር ነው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ