የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሀራ በታች  ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው – ሲኤንኤን

By Mikias Ayele

August 04, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሀራ በታች ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አምስት ግንባር ቀደም ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው አለ፡፡

በሲኤንኤን የኬንያ ተወካይ ዘጋቢ የሆነችው ቪክቶሪያ ሩባደሪ ባሰናዳችው ዘገባ÷ የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ በቡና ምርት እንደምትታወቅ እና ቡና ከኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አንስታለች፡፡

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ባደረገችው የብዝሃ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ታዳሽ ኃይል፣ በማዕድን፣ ቱሪዝም ዘርፎች እና በወሳኝ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ስኬት ማስመዝገቧን ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በተለየ መልኩ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላት አምራ እና ተውባ እንደምትገኝ በመጥቀስ፤ አዲስ አበባ ከፍተኛ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ከተማ መሆኗን ጠቅሳለች፡፡

በዓለም አቀፉ የእድገት ትንተና ማዕከል የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ መኮንን ሲኤን ኤን የሰራውን ዘገባ ተከትሎ በሰጠው አስተያየት÷ በተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያሳየች ትገኛለች ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ካሉ ምርጥ አምስት ኢኮኖሚዎች አንዱ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በወርቅ ምርት፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም እና ሌሎች መስኮች ከፍተኛ እድገት እያሳየች እንምትገኝ ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ