አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ሊፈታተኑ የሚሞክሩ ኃይሎችን ድባቅ የሚመታ ጀግና አየር ኃይል ተገንብቷል አሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፡፡
የአየር ኃይሉ የ3ኛ አየር ምድብ ላስመዘገበው የላቀ የግዳጅና የሥራ አፈጻጸም ስኬት በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው የምድቡ ጠቅላይ መምሪያ የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መከላከያ ሠራዊት በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ እያደረገ ይገኛል፡፡
አሁን የምንገኝበት ዘመን የውጊያ አካሄድና ስልት ለመገመት በሚያዳግት መልኩ በፍጥነት እየተቀያየረ ነው ያሉት አዛዡ፥ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣናም ያለው የኃይል አሰላለፍ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይልም ይህንን ታሳቢ በማድረግ የዘመኑን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል የሰው ኃይል በማብቃት፣ በርካታ ፓይለቶችን፣ ቴክኒሽያኖችንና የአስተዳደር ባለሙያዎች እያፈራ መሆኑንና የዘመኑን የውጊያ ቴክኖሎጂዎች እየታጠቀ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
3ኛ አየር ምድብም የሪፎርሙ አካል በመሆን በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ልዩ ታሪክ ያለው መሆኑንም አንስተዋል።
ምድቡ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እና ኮሎኔል ባጫ ሁንዴን የመሳሰሉ በርካታ ጀግኖችን ያፈራ መሆኑን አስታውሰው፥ አሁንም ያንን የጀግንነት ታሪክ እያደሰ በርካታ ተተኪ ወጣት በራሪዎችን በአጭር ጊዜ፣ በጥራትና በብዛት እያፈራ ይገኛል ነው ያሉት።
የሚለወጠውን የውጊያ አውድና የኃይል አሰላለፍ በመገንዘብ አመራሩና ሠራዊቱ ራሱን ከጊዜው ጋር ማዘመን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያን ሊፈታተኑ የሚሞክሩ ጠላቶችን መመከትና ድባቅ መምታት የሚያስችል ጀግና ተቋም መገንባቱን ገልጸው፥ የምድቡ አመራሮችና የሠራዊት አባላት ግዳጃቸውን በጀግንነትና በስኬት በመወጣታቸው ሊኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ታላላቅ ተልዕኮዎች እንደሚጠበቁ በመረዳት በሁሉም ረገድ ዝግጁነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡