አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ሽብርተኝነትን ለመግታት የደህንነት መረጃ ልውውጥን እና የተቀናጀ የድንበር ደኅንነት አሠራርን ማጠናከር ያስፈልጋል አሉ።
በምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ የተመራ ልዑክ በቻይና ዋይኒንግ ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብር ሴሚናር ላይ ተሳትፏል፡፡
በዚህ ወቅት ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው÷ ሽብርተኝነት ድንበር ዘለል እየሆነ መመጣቱን እና ዓለም አቀፍ አድማሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን አንስተዋል፡፡
አሁን ያለው ፈጣን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት በሽብርተኞች ዘንድ ለጥፋት ማቀጃ፣ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ፣ ለአባላት መመልመያና ጥቃቶችን በከፍተኛ ፍጥነትና ስፋት ለማስፈጸሚያነት እየዋለ መምጣቱን ገልፀዋል።
ሽብርተኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብና እየተቀያየረ የመጣ የደህንነት ስጋት መሆኑን ገልጸው÷ በሕግ አስከባሪ አካላት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ፈተና ደቅኗል ነው ያሉት፡፡
አንድ ሀገር ብቻውን ሽብርተኝነትን መግታት እንደማይችል በመግለፅ÷ ችግሩን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀረ-ሽብር ርምጃን መውሰድ፣ የደህንነት መረጃ ልውውጥን እና የተቀናጀ የድንበር ደኅንነት አሠራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በፀረ-ሽብር ትግል ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን በመጥቀስ÷ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ማካበቷን እና ይህን ልምድ ለአጋር ሀገራት ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን አብራርተዋል፡፡
መሰል ሴሚናሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተማራማሪዎችን፣ መሪዎችንና ፈፃሚዎችን በማገናኘት የምርምር ውጤቶችን፣ ልምድን እና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በባለሙያዎችና አመራሮች ዘንድ ሙያዊ ግንኙነት በመፍጠር ለፈጣን የመረጃ ልውውጥና ውጤታማ የሽብር መከላከልና መቆጣጠር ሥራ መደላድል እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ መንግሥት እና በተለይም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በፀረ-ሽብርተኝነት፣ በደህንነት እና በሕግ ማስከበር ዙርያ ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡