አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጾች የሚስተጋቡበት አሳታፊና ግልጽ የመግባባት መድረክ ነው ይህም ተስፋን የሚያለመልም ነው አሉ ተመካካሪዎች።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።
በተመካካሪዎች መካከልም አንዱ የሌላውን ሀሳብ የሚያዳምጥበትን ዕድል በመፍጠር፣ የጋራ መግባባትን የሚገነባና ተስፋን የሚያለመልም ሂደት መሆኑን ተመካካሪዎቹ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚነሱ ሀገራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ለረጅም ዘመናት ግጭት፣ ኃይልና ተቃርኖ የተለመደ መንገድ ሆኖ እንደቆየ የገለፁት ተመካካሪዎቹ፤ ምክክር አዋጭ የመፍትሔና የመግባቢያ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የሀገር ግንባታ ባህልን ለማጎልበት ዐሻራችንን የምናኖርበት ዕድል መፈጠሩ ትልቅ አጋጣሚ እና ኃላፊነት ነው ሲሉም አንስተዋል።
ጉባኤው ለቀጣዩ ትውልድ በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማስረከብ መሠረት የሚጥል የሀሳብ ሜዳ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ውጤታማ ሂደትም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና ተስፋን የሚያለመልም መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ለዘመናት ያሳለፈቻቸውን ፈተናዎች በምክክር በመፍታት በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔና መግባባት ለመገንባት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።