አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲጅታል ዘርፍ የመንግሥት አገልግሎቶችን፣ ኢኮኖሚውን እና የዜጎችን ተሳትፎ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ጉልህ የዲጂታል ሽግግር እያስመዘገበች ነው፡፡
የዲጂታል መሠረተ ልማትን፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን እና የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማጠናከር የሀገሪቱን ዲጂታል ለውጥ በተቀናጀና ዘላቂ መንገድ እያፋጠነች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ እየተከተለች በምትገኘው የዲጂታል ስርዓት ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሁም ሀገራዊ እድገትና ዘመናዊ የኢኮኖሚ ግንባታ ለማፋጠን የሚረዱ መሠረታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
በዚህም ባለፉት 5 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ተጠሪ ሆኖ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም (ፋይዳ) «ፋይዳ ቨርስ ዲጂታል ሶሉሽንስ ኢንተርፕራይዝ» በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ እንደ አዲስ ተቋቁሟል።
ይፋ በተደረገው አዲስ ተቋማዊ አደረጃጀት የሀገሪቱን የዲጂታል መሠረተ ልማት ማዕከል በማጠናከር በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር እንዲካተት ተደርጓል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ሽግግር ተቋሙ በራስ አቅም የቴክኖሎጂ ፈጠራንና ዘላቂ የፋይናንስ መሠረትን በማጣመር የፋይናንስ ነፃነትን የሚያጎለብትበትንና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን በመሳብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያረጋግጥበትን ዕድል ይፈጥራል።
ተቋሙ በፕሮጀክት ደረጃ በቆየባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የጀርባ አጥንት የሆኑ አስደናቂ ተግባራትን አከናውኗል።
እስካሁን ባለው ሂደት ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በዲጂታል መንገድ የመመዝገብ፣ ከ13 ሚሊየን በላይ የታተሙ ካርዶችን የማሰራጨት እንዲሁም ከ160 ሚሊየን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶችን የመስጠት አቅም ፈጥሯል።
በተጨማሪም ከ150 በላይ ከሚሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በቀን እስከ 2 ሚሊየን የሚደርሱ የዲጂታል ማንነት ማረጋገጫዎችን የማከናወን አቅም መገንባቱ የተቋሙን የላቀ ውጤታማነት ያሳያል።
ፋይዳ ቨርስ የኢትዮጵያ ይፋዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት ማዕከል ሆኖ በመዋቀሩ በ13 ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የዲጂታል ማንነት ሥርዓቱን ለማስተዋወቅ አስችሏል።
ይህ አደረጃጀት ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማትንና ዲጂታል አስተዳደርን ከማጠናከሩ ባሻገር የፋይናንስ አካታችነትን በማስፋትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥነ ምህዳርን በመገንባት ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ስለ ፕሮጀክት ሲገልጹ ፋይዳ ቨርስ የኢትዮጵያ ይፋዊ የዲጂታል መሰረተ ልማት እንደሚሆን እና በፈረንጆቹ 2030 የኢትዮጵያን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በ6 በመቶ እንዲያሳድግና 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያመጣ እምነት የተጣለበት መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ የፋይዳ ቨርስ መመስረት የመደመር መንግሥት የዲጂታል መሠረተ ልማት እመርታን በማሳለጥ፣ ቴክኖሎጂን ለዜጎች ሁለንተናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የተገባውን ሀገራዊ ቃል ኪዳን በተግባር ያረጋገጠ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በዮናስ ጌትነት